የኢትዮጵያ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ተመትቶ ወድቋል በሚል ምስሉ እየተዘዋወረ የሚገኘው የሰው አልባ አውሮፕላን ፎቶ ሱዳን ውስጥ የተነሳ ነው

ህዳር 5፣ 2018

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት መሀል የሚስተዋለውን ውጥረት ተከትሎ በርካታ የተሳሳቱ እና ያልተረጋገጡ መረጃዎች በተለይ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ነው።

ከእነዚህም መሀል አንድ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ንብረት የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በሁለቱ ሀገራት ድንበር አቅራቢያ ተመትቶ ወድቋል የሚል ነው።

መረጃውን ካሰራጩት ግለሰቦች በተጨማሪ ፌስቡክ ላይ ከ170 ሺህ በላይ ተከታታዮች ያሉት ‘Tigray Today’ የተባለ የፌስቡክ ገፅ ይገኝበታል። በተጨማሪም ‘ናቅፋ ፕሬስ’ የተባለ ከ118,000 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ በተመሳሳይ መረጃውን አጋርቷል።

ብዙዎቹ መረጃውን ያሰራጩ አካላት አውሮፕላኑ ቡሬ አካባቢ እንደወደቀ ገልፀው በእሳት የተያያዘ የአውሮፕላን አካል የሚመስል ፎቶ አያይዘዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት እየተቃጠለ የሚታየው አውሮፕላን ባሳለፍነው መስከረም ወር ሱዳን ውስጥ የተከሰተ መሆኑን አረጋግጧል።

‘Sudans Post’ የተባለው የዜና ድረ-ገፅ በወቅቱ እንደዘገበው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች ‘አኪንቺ’ የተባለ የቱርክ ስሪት የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን ጥለው ነበር፣ ምስሉም በዛን ወቅት የተጋራ ነበር: https://www.sudanspost.com/akinci-drone-downed-rsf-announces/#

በዚህ ዙርያ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ተመትቶ ወደቀ ስለተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን ያወጡት መግለጫም ሆነ ማብራርያ የለም።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::