የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወታደራዊ ዩኒፎረም ለብሰው የሚያሳየው የቅንብር ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

ጥቅምት 19፣ 2018
በርካታ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ የወታደራዊ ዩኒፎረም ለብሰው በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አቅራቢያ እንደተገኙ የሚያሳይ የቅንብር ምስል እያጋሩ ይገኛሉ።
ይህ በስክሪን ቅጂው የሚታየውን የቅንብር ምስል ካጋሩ መካከልም ከ29 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Sirnaaf Qabsoofna’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል።
ይህ ገጽ “ከቀይ ባህር 45 ኪሎሜትር ላይ በቡሬ ግንባር!” የሚል ጽሁፍም ከርዕሰ መስተዳድሩ የቅንብር ምስል ጋር አጋርቷል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ እንደሆነ አረጋግጧል።
የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት የጉግል ምርት የሆነውን ‘SynthID Detector’ የተጠቀምን ሲሆን ይህ መገልገያም ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈበረከ እንደሆነ አመላክቷል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚፈበረኩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቁ እና እየተበራከቱ መጥተዋል። እነዚህን አርተፊሻል ይዘቶች በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲንሸራሸሩ መመልከትም የተለመደ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ይህ ቴክኖሎጂ ሀሰተኛ መረጃን ለሚያሰራጩ ግለሰቦች እና ቡድኖች መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሲጋለጡ ይስተዋላል።
በመሆኑም አጠራጣሪ እና ታማኝ ባልሆኑ ምንጮች የሚጋሩ መረጃዎችን ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
