ጄነራል ታደሰ ወረደ ታገቱ በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ ተናገሩ

ግንቦት 21፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት የነበሩት ጄነራል ታደሰ ወረደ መታገታቸውን ወይም የቁም እስረኛ መደረጋቸውን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጠዋል።
ይህ መረጃ ባለፉት ጥቂት ቀናት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ባፈሩ የፌስቡክ ገጾች እና ግለሰቦች አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ ሲጋራ ቆይቷል።
ከመረጃው ዋነኛ አሰራጮች መካከል ወደ 480 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት “አንዳፍታ” የተሰኘው የፌስቡክ ገጽ እና ከ507 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “አባይ ሚዲያ” የፌስቡክ ገጽ ይገኙበታል። በተጨማሪም ከ161 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት “ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ” የተባለው ግለሰብ የፌስቡክ ገጽ ጄነራል ታደሰ የቁም እስረኛ እንደሆኑ የሚገልጽ ተመሳሳይ ዘገባ ከሌላ ገፅ ወስዶ አጋርቷል።
ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ እውነተኝነቱን ለማረጋገጥ በቀጥታ ከጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር በስልክ ተገናኝቶ የጠየቀ ሲሆን በማጣራቱም ጄነራሉ እንዳልታገቱና የቁም እስረኛም እንዳልተደረጉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ለዘገባቸው ዋቢ ያደረጉት «አፍሪካ ኢንተለጀንስ» (Africa Intelligence) የተሰኘው የዜና ተቋም መሆኑን ቢጠቅሱም ተቋሙ ባወጣው ዘገባ ላይ እሳቸው ስለመታገታቸውም ሆነ የቁም እስረኛ ስለመሆናቸው የጠቀሰው ነገር እንደሌለ አብራርተዋል፣ ይህንን ኢትዮጵያ ቼክም አረጋግጧል።
ጄነራል ታደሰ ወረደ ለኢትዮጵያ ቼክ በሰጡት የቀጥታ ምላሽ “ታግተሃል አልያም የቁም እስረኛ ሆነሃል ለሚለው አሁን እያናገርከኝ ነው፤ እኔ አልታገትኩም፣ የቁም እስረኛም አልተደረግኩም፤ የAfrica Intelligence ያወጣው ዘገባ ላይም እኔ እንደታገትኩም አልያም የቁም እስረኛ እንደሆንኩ አልገለጸም” ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የታዋቂ ሰዎችን እና የፖለቲካ መሪዎችን ስም በመጠቀም ያልተናገሩትን እንደተናገሩ፣ ያልሆኑትን እንደሆኑ አድርጎ ማሰራጨት የተለመደ የሀሰተኛ መረጃ ስልት መሆኑ ይታወቃል።
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መሰል አጠራጣሪ እና የፖለቲካ ትኩሳት ያላቸውን መረጃዎች ሲያነቡ መረጃው የወጣበትን ድረ-ገጽ ታማኝነት እንዲያረጋግጡ እና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከማጋራት እንዲቆጠቡ እንመክራለን።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





