የሩስያው የዜና ወኪል ያሰራጨው ምስል በኢትዮጵያ ሊገነባው የታቀደውን የኤርፖርት ንድፍ አያሳይም

የሩስያው የዜና ወኪል ያሰራጨው ምስል በኢትዮጵያ ሊገነባው የታቀደውን የኤርፖርት ንድፍ አያሳይም

ግንቦት 7፣ 2017

ስፑትኒክ የተባለው የሩስያ የዜና ወኪል (Sputnik Ethiopia) በተባለ የኤክስ (ትዊተር) አካውንቱ ላይ አንድ ምስል በዛሬው እለት አጋርቶ ነበር።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ቢሮውን የከፈተው የዜና ወኪሉ ምስሉ ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ማዕከል ለመሆን ካላት ግብ ጋር የተያያዘ መረጃ አጋርቶ ነበር።

ከዚህ በፊትም በርከት ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እና የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችም በስክሪን ቅጂው ላይ የሚታየውን ምስል አየር መንገዱ ሊገነባ ያቀደውን ‘ኤርፖርት ሲቲ’ የሚያሳይ ንድፍ መሆኑን በሚገልጽ መልኩ ሲያጋሩ ተመልክተናል።

ሌሎች ደግሞ ከሌላ ድረ-ገጾች ወይም ሌላ ምንጮች የተወሰዱ መሆናቸውን ሳይገልጹ ምስሎቹን ከመረጃው ጋር እያጋሩ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ስፑትኒክ ያጋራው ምስል አሳሳች መሆኑን ያደረግነው የምስል ፍተሻ ያሳያል።

ምስሉ በደቡብ ኮርያ ‘ኢንችዮን’ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሊሰራ የታቀደ ኤርፖርትን እንደሚያሳይ ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ (https://www.archdaily.com/433754/incheon-international-airport-terminal-2-gensler)

ይህ የ2.5 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት 72 በሮች ያሉት ሲሆን የከተማዋን ኤርፖርት አቅም በእጥፍ ያሳድገዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‘በአፍሪካ ትልቁ አየር ማረፊያ’ የተባለውን ‘ኤርፖርት ሲቲ’ ግንባታ እቅድ ይፋ ካደረገ ሰነበብቷል።

የዛሬ ሁለት አመት ገደማ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በድረ-ገጹ ባጋራው ዜና ተቋሙ ‘የኤርፖርት ሲቲ’ ግንባታዉን በ2015 በጀት አመት ለመጀመር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የድርጅቱን ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር፡ https://www.ena.et/web/amh/w/am_197074

ሰሞኑንም አየር መንገዱ ግንባታውን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ እየተዘገበ ይገኛል።

ትክክለኛ ለሆኑ መረጃዎች አሳሳች ምስሎችን መጠቀም ለተዛባ መረጃ ስለሚያጋልጥ ጥንቃቄ እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::