ይህ ምስል “በአክሱም ሆስፒታል ሀኪሞች ስራ በማቆማቸው ህይወታቸው ያለፈን አዛውንት” አያሳይም!

ይህ ምስል “በአክሱም ሆስፒታል ሀኪሞች ስራ በማቆማቸው ህይወታቸው ያለፈን አዛውንት” አያሳይም!

ግንቦት 5፣ 2017

በርካታ የፌስቡክ ገጾችና አካውንቶች ምስላቸው የሚታየው አዛውንት በትላንትናው እለት በአክሱም ሆስፒታል ህይወታቸው እንዳለፈ መረጃ እያጋሩ ይገኛሉ።

ይህ መረጃ “የህልፈታቸው ምክንያት ደግሞ ሀኪሞች የስራ ማቆም ሰልፍ በግቢ ውስጥ እያካሄዱ ስለነበር ነው” ይላል።

በተጨማሪም “በመጨረሻም የድንገተኛ ክፍል ተረኛ የነበረው ሀኪም ጋወኑን አውልቆ ጠቅልሎ በላያቸው ላይ ጥሎ ዳግም ወደ ህክምና ላይመለስ እያለቀሰ ግቢውን ለቆ ወጣ” የሚል መረጃም ተካቷል።

ይህን መረጃ ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘Kalkidan Dawit’ የሚል ስም እና 45 ሺህ ተከታዮች ያሉት ገጽ ይገኝበታል።

በዚህ ገጽ የተጋራውን መረጃ ከ100 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው ያጋሩት ሲሆን ከ340 በላይ አስተያየቶች ተሰጥተውበታል፣ ከ1,500 በላይ ሰዎች ደግሞ ሪአክሽን ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ይህ ምስል በትላንትናው እለት በአክሱም ሆስፒታል ህይወታቸው ያለፈን አዛውንትን እንደማያሳይ አረጋግጧል።

ምስልን በምልሰት መፈለጊያ መገልገያዎችን በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሉ ከ6 ቀናት በፊት ፌስቡክ እና ኤክስ (X) ላይ ተጋርቶ እንደነበር ተመልክተናል።

ምስሉን ያጋሩ አካውንቶች በትግራይ ክልል ሕፃፅ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃይን እንደሚያሳይ በመግለጽ በከተማው የሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ይህን ከቀናት በፊት የተጋራ ምስልና መረጃም ቀጥሎ ያሉትን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን መመልከት ይቻላል፡ https://www.facebook.com/share/p/1AafEVYpJC/ እና https://x.com/tigrwayti/status/1919738488661881344?s=46&t=dmcdufxK8i9nmLEWi2-yGQ

በሌላ በኩል በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች እና ከተሞች የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ላለፈው አንድ ወር ከደሞዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ጋር በተገናኘ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ከዛሬ ግንቦት 5፣ 2017 ጀምሮ ደግሞ ስራ የማቆም አድማ እንደሚያደርጉ ሲገልጹ ሰንብተዋል።

በዚህ ጊዜያት በርካታ መረጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጋሩ ሲሆን ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች እንዳንጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::