የሶማሊያ መንግስት ለአልሸባብ አንድ ሄሊኮፕተር ሙሉ መሳርያ ሰጠ” ከሚል መረጃ ጋር ተያይዞ የተጋራው ምስል አሳሳች ነው

ጥቅምት 04 2017 ዓ.ም

የሶማልያ መንግስት በአገሪቱ ለሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ታጣቂ ቡድን የጦር መሳሪያ ሰጠ የሚል መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጋርቷል።

ለምሳሌም ይህ ከ11 ሺ በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Habtish Gurmu’ የሚል ስያሜ የሚጠቀም የኤክስ (ትዊተር) አካውንት ጉዳዩን ከአንድ የጦር ሄሊኮፕተር ምስል ጋር በማያያዝ አቅርቧል።

አካውንቱ “የሶማሊያ መንግስት ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ሄሊኮፕተር ሙሉ የጦር መሳሪያ ለአልሸባብ ሰጠ” ብሎ መረጃ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ ቼክ የምስሉን ምንጭ ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ ቲንአይ (TinEye) እንዲሁም ያንዴክስ (Yandex) የተባሉ የምስል ማሰሻዎች/ማጣርያዎች ተጠቅሟል።

በዚህም መሰረት በፎቶው ላይ የሚታየው ሄሊኮፕተር ንብረትነቱ የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ሲሆን እ.ኤ.አ ጥቅምት 4/ 2012 ዓ.ም የተወሰደ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።

ፎቶው ‘አላሚ ፎቶስ’ የተባለ የምስሎች ክምችት በሚያቀርብ ድርጅት ድረ-ገፅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የኬንያ አየር ሃይል ሄሊኮፕተር በደቡብ ሶማሊያ ኪስማዮ አየር ማረፊያ ማረፉን የሚያሳይ እና የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመረጃ ድጋፍ ጥምረት ያጋሩት ምስል እንደሆነ ይጠቅሳል።

ትክክለኛውን ፎቶም ይህን ማስፈጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል፡ https://www.alamy.com/stock-photo-somalia-kismayo-in-a-handout-photograph-released-by-the-african-union-115380881.html

አልሻባብ ሶማሊያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ታጣቂ ቡድን ሲሆን ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በይፋ ይናገራል። አብዛኛው ማዕከላዊ እና ደቡባዊ የሶማሊያ ክፍል ቡድን ቁጥጥር ሥር ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የሶማልያ መንግስት ለዚህ ታጣቂ ቡድን የሰጠው የመሳሪያ ድጋፍ ስለመኖሩ የሚገልጹ መረጃዎችም የሉም። የሶማሊያ መንግሥት ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አልሸባብ የተሰኘው ቡድን ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠሉን ሲገልጽ ቆይቷል።

ጊዜያቸውን ባልጠበቀና ከአውድ ውጭ በሆነ መልኩ የሚጋሩ ፎቶዎች ለሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ጥንቃቄና ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::