የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ

ሐምሌ 22፣ 2016 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን መግለጹ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ጉዳዩ የማህበራዊ ሚዲያ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ተመልክተናል።
ሆኖም አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች አሳሳች መረጃዎችን ሲያሰራጩ ተመልክተናል። ከነዚህም መካከል “ያሻህን ዶላር ብትይዝ የሚናገርህ የለም… ባንክ ያለህን ብር በሙሉ በዶላር መቀየር ትችላለህ” የሚሉ ይገኙበታል።
ነገር ግን እንዲህ ያሉ መረጃዎች ትክክለኛ አይደሉም።
ይህንንም ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት በተመለከተ ዛሬ ንጋት ላይ በድረገጹ ባጋራው ባለ 108 ገጽ ዝርዝር መመሪያ መመልከት ይቻላል። በመመሪያ የውጭ ምንዛሬን ማን፤ መቼ፤ እንዴት፤ ለምን… መያዝ፤ መሸጥ እንዲሁም መግዛት እንደሚችል ይዘረዝራል። ቅጣቶችንም ያስቀምጣል።።
ከድንጋጌዎቹ መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል:
– ከኢትዮጵያ ወደ ሌላ ሀገር የሚጓዝ ወይም ከሌላ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሰው ከ3,000 የኢትዮጵያ ብር በላይ በጥሬው መያዝ አይችልም።
– ወደ ጅቡቲ ወይም ወደሌላ የጎረቤት ሀገር ወደብ ከተሞች የሚጓዝ ሰው እስከ 10,000 የኢትዮጵያ ብር መያዝ ይችላል።
– በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ሰው ወደ ግዛት ክልሏ ሲገባ በጉዞ ሰነዱ ላይ በስደተኞችና በዜግነት አገልግሎት ማህተም ተረጋግጦ የገባበት ቀን ተብሎ ከሚጠቀሰው ቀን አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ የያዘውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ፍቃድ ባላቸው የምንዛሪ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት የመመንዘር ወይም በባንክ በስሙ በተከፈተ የውጭ ምንዛሪ ሂሳብ ገቢ የማድረግ ግዴታ አለበት።
– ሆኖም ግለሰቡ የያዘው ሊመነዘር የሚችል የውጭ ሀገር ገንዘብ ከ10,000 የአሜሪካን ዶላር እኩል ወይም በላይ ከሆነ የውጭ ሀገር ገንዘቡ በውጭ ሀገር ምንዛሪ የባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረግ አለበት። ገቢ ሲያደርግም የጉምሩክ ዲክላሬሽን ወይም ወደ ሀገር የገባ የውጭ ሀገር ገንዘብ ማሳወቂያ መግለጫ ሰነድ ማቅረብ አለበት።
– ግለሰቡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ሀገር ዜጋ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ማይኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆነና ከዘጠና ቀናት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የመቆየት ሀሳብ ካለው፤ የያዘውን የውጭ ሀገር ገንዘብ በሙሉ በጉዞ ሰነዱ ላይ ከሚጠቀሰው ወደ ሀገር የገባበት ቀን ጀምሮ በዘጠና ቀናት ውስጥ በውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳቡ ገቢ ማድረግ አለበት።
– ከ10,000 ዶላር በላይ የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዞ ከሆነም ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ ሂሳቡ ገቢ ሲያደርግ ወይም በሕጋዊ መልኩ ሲመነዝር የጉምሩክ የውጭ ምንዛሪ ማሳወቂያ ሰነድ ማቅረብ አለበት።
– ወደ ውጭ ሀገር የሚጓዝ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሰው ከተፈቀደላቸው የምንዛሪ አገልግሎት ሰጪዎች የገዛው የውጭ ሀገር ገንዘብ ካለ የገዛበት ደረሰኝ ላይ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለ30 ቀናት ይዞ ማቆየት ይችላል።
– ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ከሚጋሩ የጎረቤት ሀገራት በየብስ መጓጓዣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ማንኛውም ሰው በድንበር ላይ ላለ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ወይም ጣቢያ ከ500 የአሜሪካ ዶላር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ወይም ከዛ በላይ ሌላ የውጭ ሀገር ገንዘብ ከያዘ የያዘውን የገንዘብ መጠን የጉምሩክ የውጭ ምንዛሪ ማሳወቂያ መግለጫ ላይ በመሙላት ማሳወቅ ያለበት ሲሆን፤ ይህንኑ ያሳወቀውን የውጭ ሀገር ገንዘብ መጠንም ጉዳዩን ጨርሶ ሲመለስ ይዞ መውጣት ይችላል።
– በብሔራዊ ባንክ ወይም አግባብ ባለው ሕግ ካልተፈቀደለት በስተቀር ማንኛውም ሰው የውጭ ሀገር ገንዘብ በጥሬው በስጦታም ሆነ በእርዳታ ወይም ለግብይት ክፍያ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ወይም መክፈል አይችልም።
– በብሔራዊ ባንክ ፍቃድ በዚህ መመሪያ ወይም በሌላ ሕግ በተፈቀደው መሰረት ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ መያዝ አይፈቀድም።
መመሪያው ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ዝርዝሮች የያዘ ሲሆን ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ሙሉውን ማንበብ ይቻላል: https://nbe.gov.et/fx/
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
