ይህ ምስል በፋኖ ታጣቂዎች የተደመሰሱ የሱማሌላንድ ሚሊሻዎችን አያሳይም

ሐምሌ 13፣ 2016 ዓ.ም
ከ14,200 በላይ ተከታታዮች ያሉትና ‘HODAN HOMES’ የሚል ስያሜ የሚጠቀም የኤክስ (ትዊተር) አካውንት በኢትዮጵያ እየሰለጠኑ የሚገኙ በርካታ የሱማሌላንድ ሚሊሻዎች በፋኖ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን የሚገልጽ መልዕክት ማጋራቱን ተመልክተናል።
ከመልዕክቱ ጋርም ተደመሰሱ የተባሉትን የሱማሌላንድ ሚሊሻዎችንና የፋኖ ታጣቂዎችን ያሳያሉ ያላቸውን ምስሎች ማያያዙን አስተውለናል፣ በዚህም በርከት ያለ ግብረ-መልስ አግኝቷል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት የተደመሰሱ የሱማሌላንድ ሚሊሻዎችንና የፋኖ ታጣቂዎችን ያሳያሉ ተብለው የተጋሩት ምስሎች ከአውድ ውጭ የተወሰዱ መሆናቸውን አረጋግጧል።
የተደመሰሱ የሱማሌላንድ ሚሊሻዎችን ያሳያል ተብሎ የቀረበው ምስል እአአ ከ1998-2000 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገው የድንበር ይገባኛል ጦርነት ወቅት የተነሳ ምስል ሲሆን ቀደም ባሉት አመታት በበርካታ ድረ-ገጾችና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሲጋራ የነበረ ነው። ከአመታት በፊት ምስሉን ካጋሩ ድረገጾች መካከል ይህንን መመልከት ይቻላል: https://www.eritreadigest.com/eritrea-ethiopia-put-their-war-masks-on/
የአማራ ፋኖ ታጣቂዎችን ያሳያል ተብሎ የተጋራው ምስል በአንጻሩ በአቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አማካኝነት የተፈበረከ ሲሆን ምስሉም ባለፉት ወራት በበርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሲዘዋወር የነበረ ነው።
ባለፉት ሳምንታት በርከት ያሉ የሱማሊያ እና የሱማሌላንድ ራስገዝ አስተዳደርን በተመለከተ የሚዘግቡ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች የሱማሌላንድ ምልምል ወታደሮች ለስልጠና ወደ ኢትዮጵያ መላካቸውን የሚገልጹ መረጃዎችን ሲያጋሩ መቆየታቸውን ይታወቃል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
