አንድ የሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግስት ባለስልጣን የአሜሪካ ልዩ ልኡክን በተመለከተ ያጋሩት መረጃ ተቀናብሮ የተሰራ ነው

mike hammer

ነሐሴ 01፣ 2016 ዓ.ም

የሱማሌላንድ ራስ ገዝ መንግስት የንግድና ቱሪዝም ሚኒስትር ዋና ዳሬክተር አብዲራሽድ ኢብራሂም በኤክስ/ትዊተር አካውንታቸው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ አምባሳደር ማይክ ሀመር ተናግረውታል ያሉትን መረጃ ከጋዜጣ የተወሰደ የሚመስል ምስል በማያያዝ ማጋራታቸውን ተመልክተናል።

ዋና ዳሬክተሩ ባጋሩት በዚሁ መረጃ አምባሳደር ማይክ ሀመር የሱማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ አንጻር የተከተሉት የዲፕሎማሲ አካሄድ “ይበል የሚያሰኝ ነው” ማለታቸውን ገልጸዋል። ለመረጃቸው ማጣቀሻም “The African Herald Journal” ከተባለ ጋዜጣ ወሰድኩት ያሉትን ምስል አያይዘዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት አምባሳደር ማይክ ሀመር እንዲህ ያለ ንግግር የትም ቦታ አለማድረጋቸውን ያረጋገጠ ሲሆን ለማጣቀሻነት የቀረበው የጋዜጣ ምስልም ተቀናብሮ የተሰራ መሆኑን አረጋግጧል።

ዋና ዳሬክተሩ በማስረጃነት የጠቀሱት ጋዜጣ በነባራዊው አለም የሌለ መሆኑን ባደረግነው ፍተሻ ከማረጋገጣችንም በላይ በቅንብር የተሰራው ምስልም በርከት ያሉ የዲዛይን አላባዊያን (design elements) እና የይዘት ስህተት ያለበት መሆኑን ተመልክተናል።

ለምሳሌም ዋና ዳሬክተሩ ባያያዙት የጋዜጣ ምስል አምባሳደር ማይክ ሀመር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ማጠናቀቃቸው ያስነብባል፣ ይህ ስህተት ነው።

በተጨማሪም በቀረበው የጋዜጣ ምስል በማሟያነት የቀረበው ሁለተኛው ዜና (International Moose Count Underway: By Bob O’Bobston) የሚለው እአአ በ2020 ዓ.ም ከታተመው “Hat” ጋዜጣ የተወሰደ መሆኑን አረጋግጠናል። ይህንንም የሚከተለውን ማስፈንጠሪያ በመከተል መመልከት ይቻላል: https://www.scribd.com/document/476314698/Hat

እንዲሁም የዜናው ጸሃፊ ስም (byline) “አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ” በሚል የቦታ ጠቋሚ ስም  መተካቱን በስህተትነት መጥቀስ ይቻላል።

በተመሳሳይ በትናንትናው እለት ‘ዳጉ ሚድያ’ የሚል ስያሜ ባለው የዩትዩብ ቻናል ላይም አምባሳደር ማይክ ሀመር ጎጃም እንደገቡ እና “ከዘመነ ጋር መከሩ” የሚል ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭቶ እንደነበር ትናንት አስነብበን ነበር።

አምባሳደር ማይክ በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመውን የሠላም ስምምነት ተግባራዊነትን በሚገመግመው የአፍሪካ ኅብረት ሁለተኛ ስብሰባ ላይ ለመታደም ወደ አፍሪካ ቀንድ ማምራታቸውን ሚዲያዎች መዘገባቸው ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::