የአልባንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤዲ ራማ አሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረት እና እስራኤል “ሰይጣን ናቸው” አላሉም

የአልባንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤዲ ራማ አሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረት እና እስራኤል “ሰይጣን ናቸው” አላሉም

ሰኔ  21፣ 2016

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ልማት  ዘርፍ  ሚኒስትር ዴታ የሆኑት ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) የአልባንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤዲ ራማ አሜሪካ፣ ሶቭየት ህብረት እና እስራኤልን “የአለማችን ሶስቱ ዋና ሰይጣኖች” ብለዋል ሲሉ በተረጋገጠ የኤክስ (X) አካውንታቸው መረጃ አጋርተው ነበር።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በመረጃው ዙርያ ባደረገው ማጣራት ሚኒስትር ዴታው ያጋሩት መረጃ ከአውድ ውጭ የተጋራና አሳሳች መሆኑን መረዳት ችለናል።

የዚህ መረጃ መነሻ የአልባንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤዲ ራማ እና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የካቲት 7፣ 2016 አልቤንያ ቲራና ውስጥ በጋራ የሰጡት መግለጫ ነው።

በመግለጫው የአልባንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው በኮሚኒስት አገዛዝ ትመራ በነበረበት ወቅት የወቅቱ አገዛዝ ለሶስቱ ሀገራት የነበረውን አመለካከት ነበር የጠቆሙት።

የወቅቱ የአልባንያ “አገዛዝ በአሰቃቂ ሁኔታ የሶስቱ ዋና ሰይጣኖች ተቃዋሚ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስ (አሜሪካ)፤ ሶቭየት ህብረት እና እስራኤል” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የተናገሩት የሀገራቸውን ወይም የእርሳቸውን ወቅታዊ አቋም ሳይሆን ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እስከ መጨረሻ የነበረውን የኮሚኒስት አገዛዝ አመለካከት ነው።

የጠቅላይ ሚኒሰትር ኤዲ ራማ እና አንቶኒ ብሊንከን ሙሉ መግለጫም የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ መ/ቤት ድረ-ገጽ ላይ የሚገኘ ሲሆን የጠ/ሚኒስትሩ ንግግርም በዚህ የዩትዩብ ቪዲዮ ከ50ኛ ደቂቃ ጀምሮ ይገኛል፡ https://www.youtube.com/watch?v=9z5OHgNDwvg&t=2979s

ሚኒስትር ዴታው ይህ ስክሪን ቅጂው የሚታየውና በምስል የተደገፈ መረጃ ካጋሩ በኋላ መልሰው አጥፍተውታል።

ከአውድ ውጭ የሚጋሩ መረጃዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና ማጋራታችን በፊት ተገቢውን ጥንቃቄና ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::