ኤርትራ በኢትዮጵያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለዘለቄታው ዘግታለች በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው

ሰኔ 12፣ 2016 ዓ.ም

ከ22,500 በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Dagmawi M. Belay’ የሚል ስም የሚጠቀም ማረጋገጫ (verification) ያለው የኤክስ (ትዊተር) አካውንት ኤርትራ በአዲስ አበባ የሚገኘውን ኤምባሲያዋን መዝጋቷል የሚገልጽ መረጃ ማጋራቱን ተመልክተናል።

ከመረጃው ጋርም ኤምባሲው ለዘለቄታው መዘጋቱን (Permantly Closed) የሚገልጽ  ከጎግል ማፕ የተወሰደ የስቅሪን ቅጅ አያይዟል።

ይህን መረጃ ከላይ ከተጠቀሰው አካውንት በተጨማሪ በርከት ያሉ የቲክቶክና የዩቱብ ቻናሎች በሰበር ዜና መልክ ሲያቀርቡት ተመልክተናል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ስለኤምባሲው መዘጋት የተሰራጩ መረጃዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የኤርትራ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ  (Chargés d’affaires en pied ) ቢኒያም በርሄ ኤምባሲው ክፍት መሆኑን አረጋግጠውልናል።

በተጨማሪም ኤምባሲው የተለመደ ስራውን በመከወን ላይ መሆኑን የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎችን የተመለከተን ሲሆን ለምሳሌም በትናንትናው እለት አቶ ቢኒያም በርሄ የቀድሞውን የሲሸልስ ምክትል ፕሬዝደንት በኤምባሲው ተቀብለው እንዳነጋገሩ ኤምባሲው በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ አስታውቋል።

በጎግል ማፕ ላይ ይታይ የነበረው “permanently Closed” የሚለው ጽሁፍም መስተካከሉን ተመልክተናል። ጎግል መረጃውን እንዲያስተካክል ኤምባሲው እና ጉዳይ አስፈጻሚው ባለፉት ቀናት የኤክስ አካውንታቸው በመጠቀም አቤቱታ ሲያቀርቡ ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::