በትናንትናው እለት ወደ አክሱም የበረረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አርማ (livery) ለምን አልነበረውም?

በትናንትናው እለት ወደ አክሱም የበረረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አርማ (livery) ለምን አልነበረውም?

ሰኔ  3፣ 2016

በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ወደ አክሱም ከተማ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ በትናንትናው እለት መጀመሩ ይታወቃል። በዚህ በረራ ላይ አየር መንገዱ ቦይንግ 737-700 አውሮፕላን የተጠቀመ ሲሆን 140 ተጓዦችን ይዞ ወደ አክሱም ተጉዞ ነበር።

ይሁንና አውሮፕላኑ የተለመደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማ ወይም ቅብ (livery) ስላልነበረው በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ አጭሯል፣ ሴራ ትንተና አስከትሏል እንዲሁም መላ ምቶችን አስተናግዷል። በርካታ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም ጉዳዩን እንድናጣራ ጥያቄ አቅርበዋል።

ከአየር መንገዱ እና በረራውን ካስተባበሩ አካላት ያገኘነው የተረጋገጠ መረጃ እንደሚያሳየው የአየር መንገዱ ጥቂት የሚባሉ ቦይንግ 737 እና Q-400 (Bombardier) አውሮፕላኖች ነጭ ቀለም ተቀብተው ይገኛሉ።

ይህም የሚሆነው ስራን ለማቀላጠፍ ነው። እንዴት?

አየር መንገዱ የቶጎ፣ ማላዊ እና ዛምቢያ አየር መንገዶች ላይ ሼር ይዟል። ስለዚህ እነዚህ አየር መንገዶች አውሮፕላኖቻቸውን ለጥገና ወደ ኢትዮጵያ ሲያመጡ እነዚህ ነጭ የተቀቡ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን አርማ ያልያዙ አውሮፕላኖች በምትክነት ይላካሉ፣ ምክንያቱም የተለዩ አየር መንገዶች ስለሆኑና የኢትዮጵያ አየር መንገድን አርማ መጠቀም ስለማይችሉ። አየር መንገዱ በዚህም የራሱን ጥቅም ያገኛል።

የአየር መንገድ ምንጭ ይህን ሲያብራሩ “ይህ ነጭ ብቻ የተቀባ አውሮፕላን ትናንት በአጋጣሚ በበረራ ስምሪት ክፍል የተመረጠ ነው፣ ለምሳሌ ዛሬ ባለው በረራ እሱ አውሮፕላን ሳይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማ ያለው ወደ አክሱም ይበራል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ የኢንተርኔት ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን ይህ አሰራር በአለም ዙርያ የተለመደ እንደሆነ ማየት ችሏል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::