ይህ ቪድዮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀረፀ አይደለም፣ ለሽያጭ ቀረቡ የተባሉ ሴቶችንም አያሳይም

A false message shared on Twitter referring "Muslim women's market in Ethiopia"

ነሐሴ 24፣ 2015 ዓ.ም

በስክሪን ቅጂው ላይ የሚታየውና “በኢትዮጵያ የሙስሊም ሴቶች ገበያ” ከሚል ጽሁፍ ጋር በትዊተር (አሁን ላይ ኤክስ ተብሎ በሚጠራው) ላይ የተጋራ ቪዲዮ በርካታ መስተጋብሮችን እያስተናገደ መሆኑን ተመልክተናል።

ቪዲዮውን በትዊተር አካውንታቸው ያጋሩት ደግሞ የኔዘርላንድስ (ሆላንድ) ፓርላማ አባል እንዲሁም የነጻነት ፓርቲ (PVV) ሊቀመንበር የሆኑት ሂርት ዊልደርስ (Geert Wilders) ናቸው፡ https://x.com/geertwilderspvv/status/1695757261224694160?s=46&t=dmcdufxK8i9nmLEWi2-yGQ

ይህ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታታዮች ባሉት የፖለቲከኛው የተረጋገጠ (verified) የትዊተር አካውንት የተጋራው ቪድዮ ከ213 ሺህ በላይ እይታዎችን አግኝቷል፤ ከ800 በላይ የትዊተር ተጠቃሚዎችም መልሰው አጋርተውታል። በተጨማሪም በርካታ የትዊተር ተጠቃሚዎች ሀሳብ እና አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል።

ሌላ ቡርሂ (Burhi) የሚል ስምና ከ100 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የተረጋገጠ የትዊተር አካውንትም ቪድዮውን ያጋራ ሲሆን “በ2023 አፍሪካ ውስጥ ያለ የባርያ ገበያ። ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ተብሏል” የሚል ጽሁፍም አብሮ አጋርቷል፡ https://x.com/burhimum/status/1691841437133164726?s=48&t=dmcdufxK8i9nmLEWi2-yGQ

ኢትዮጵያ ቼክ በቪድዮው ላይ ባደረገው ማጣራት ቪድዮው ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀረጸ እንዳልሆነ አረጋግጧል። ነጭ ልብስ ለብሰው በቪድዮው የሚታዩት ለሽያጭ የቀረቡ ሰዎች እንደሆኑ የሚገልጹት የጽሁፍ መረጃዎችም ሀሰት መሆናቸውን ተመልክተናል።

ይህ ቪድዮ በአፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል ውስጥ ጂላስ (Djilasse) የምትባል መንደር ውስጥ የተቀረጸ ሲሆን ንዱት (Ndut) በመባል ለሚታወቅ ባህላዊ ሥነ ስርዓት የተሰበሰቡ የመንደሩን ነዋሪዎችን የሚያሳይ ነው።

ይህ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ስርዓት በሴኔጋል፤ ጋምቢያ እና ሞሪታንያ በሚገኙት የሰረር (Serer) ህዝቦች የሚከወን ሲሆን ልጆች ወደ ወጣትነት (ጉርምስና) የሚሸጋገሩበት ነው።

በዚሁ መሰረት በቪድዮው በነጭ ልብስ ተሸፍነው የሚታዩት ከልጅነት ወደ ወጣትነት (ጉርምስና) በመሸጋገር ላይ ያሉ የሰረር ወንድ ልጆች ናቸው።

ይህን በጂላስ (Djilasse) መንደር የተከናወነ ስርዓት የሚያሳዩ ቪድዮዎችም በቲክቶክ እና ዩትዩብ የተጋሩ ሲሆን ይህ ከ8 ወራት በፊት የተጋራ የዩትዩብ ቪድዮ የባህላዊ ስርዓቱን ሂደት በደንብ የሚያሳይ ነው፡ https://www.youtube.com/watch?v=nlRp1pzvwmQ

ስርዓቱ ከሌላ አቅጣጫ ተቀርጾ የሚያሳይ ቪድዮም ከ8 ወራት በፊት በቲክቶክ ተጋርቶ የነበረ ሲሆን በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡ https://www.tiktok.com/@lang.simal.tv/video/7181753490769825030

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::