በመሻሻል ላይ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ የሜትር ታክሲዎችን ይመለከታል?

vat proclamation under revision and meter taxis

ሰኔ 29፣ 2015

ከዓመት በፊት በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መሥሪያ ቤታቸው ለ2015 በጀት ዓመት ያዘጋጀውን በጀት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ የታክስ ገቢን ለመጨመር የህግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ተናግረው ነበር። ማሻሻያ ከሚደረግባቸው ህጎች መካከል የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ አንዱ እንደሆነ ገልጸው ነበር።

ሚንስትሩ ይህን ከተናገሩ ከወራት በኃላ ረቂቅ ህጉ ለውይይት መቅረቡ በሚዲያዎች የተዘገበ ሲሆን ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ከቫት ነፃ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት በረቂቅ ህጉ ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠውለት ወደ ተጨማሪ እሴት ታክስ ስርዐት እንደሚገባ ተነግሮ ነበር። በዚህም ባለሦስት እግር ተሽከርካሪን ሳይጨምር፣ ከእነ ሾፌሩ ከስምንት ሰው በታች የመጫን አቅም ያላቸው ታክሲዎች፣ ተሽከርካሪዎች ማከራየት፣ ከእነ ሾፌሩ የሚሰጥ የኪራይ ተሽከርካሪ አገልግሎት፣ እንዲሁም ቱሪስቶችን የማጓጓዝ አገልግሎት ከቫት ነፃ አይሆኑም። (ዝርዝሩን ይመልከቱ: https://www.ethiopianreporter.com/108610/ )

ረቂቅ ህጉ የሚጸድቅ ከሆነ በተለምዶ “ራይድ” ተብሎ የሚጠራውን የሜትር ታክሲ አገልግሎት ላይ ተጽኖ ሊያሳድር እንደሚችል በዘርፉ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጭዎች ስጋታቸውን ሲገልጹም ተስተውሏል። የዛይራይድ እና የዊዝ ድርጅቶች ስጋታቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ከገለጹት መካከል ይገኙበታል። (ዝርዝሩን ይመልከቱ: https://www.thereporterethiopia.com/25224/ )

በአመቱ አጋማሽ ረቂቅ ህጉ ለህዝብ ውይይት መቅረቡንም ሚዲያዎች በስፋት ሲዘግቡ ተስተውሏል። የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎችም ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንደሆኑ በዘገባዎቹ ተካቷል።

ይህ በእንዲህ እያለ “Ride Drivers Update” የተባለና ከ27 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም ቻናል ከቀናት በፊት “ታላቅ የምስራች” በሚል ርዕስ ስር “ራይድ ከገንዘብ ሚኒስቴር ሚንስትር ጋር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ጋር ባደረገው ረጅም ጊዜ የፈጀ የጋራ ስራ እነሆ ከራይድ ጋር የሚሰሩ አከርካሪዎች የተራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ታምኖበት የሚከፍሉት ግብር ከToT እና ቫት ነጻ እንዲሆን መወሰኑን በታላቅ ደስታ እናበስራለን” የሚል መረጃ አጋርቷል። የመረጃውን ትክክለኛነት እንድናጣራላቸውም ተከታታዮቻችን ጠይቀውናል።

ኢትዮጵያ ቼክ በቴሌግራም ቻናሉ የቀረበውን መረጃ በተመለከተ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮን አነጋግሯል።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ እንዳለ ከበደ “በቴሌግራም ቻናሉ የቀረበው መረጃ ትክክለኛ ነው” የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን ዝርዝር መረጃ ለጊዜም መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ረቂቅ አዋጁ በሚንስትሮች ምክር ቤት ስለመጽደቁ በምክር ቤቱ የተሰጠ መግለጫ አለመኖሩንም ተመልክቷል። የሚንስትሮች ምክር ቤት ያጸደቃቸውን አዋጆች  በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ በየጊዜው እንደሚገልጽ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::