የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የተቋሙና የአ/አ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ለኢትዮጵያ ቼክ የሰጡት ማብራሪያ

ሰኔ 13፣ 2015
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ወቅታዊ ሁኔታን እንድናጣራላቸዉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡልን ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ቼክ ‘የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ህጋዊነትና ‘ሮስካ’ የክፍያ አማራጭ ጉዳይ’ በሚል ርዕስ ከአመት ከ8 ወር በፊት ባጋራዉ መረጃ ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ (የማህበር ቤት ልማት) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እውቅና ያለው ህጋዊ ተቋም መሆኑን ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አመራሮች ያገኘዉን መረጃ አጋርቶ ነበር፡ https://t.me/ethiopiacheck/868
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ሮስካ የክፍያ አማራጭን በተመለከተ ‘በየሶስት ወሩ ይወጣል የተባለዉ እጣ እየወጣ አይደለም፤ ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ መረጃ እያገኘን አይደለም እንዲሁም አሁን ስላለበት ሁኔታ ማወቅ አልቻልንም’ የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ ቼክ የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪ እንዲሁም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኢንጂነር መኮንን ሚጀናን አናግሯል።
ኢንጂነር መኮንን ሚጀና ቢሯቸዉ ከጎጆ ብሪጅ ሀዉሲንግ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እየሰሩ እንደሚገኙ ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።
ነገር ግን ቢሯቸዉ ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ጋር እየሰራ የሚገኘዉ መደበኛዉ ሞዴል ላይ እንደሆነ የሚናገሩት ኢ/ር መኮንን ሮስካ የከፍያ አማራጭ በቢሯቸዉ ተገምግሞ ዉሳኔ እንዳልተሰጠበት ነግረዉናል።
“የሮስካ ገና ተገምግሞ አላለቀም። እነሱ ያቀረቡበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ተገምግሞ የመጨረሻ ዉሳኔ አልተነገራቸዉም። መጀመሪያ ይሄኛዉን (መደበኛዉን) ወደ ትግበራ እንዲገቡ ነው አሁን የጀመሩት” ብለዋል።
የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪ በበኩላቸዉ ሮስካ “ከመደበኛዉ ጋር ብዙ ልዩነት የለዉም። ከአንድ ቋት አዉጥቶ የመስራት ጉዳይ ነው እንጂ ዞሮ ዞሮ ሄዶ ከባለ ይዞታ እና ከጎጆ ጋር ነው የሚገናኘው። የአከፋፈል ስልት ብቻ ነው የቀየርነው። ይሄንን ደግሞ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ሁለት ጊዜ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተናል። እና አመራሩም ባለበት የተማመንበት ነው የሚመስለኝ እንጂ ብዙ ነገር የቀረ ያለ አይመስለኝም” ሲሉ መልሰዋል።
ሮስካ የክፍያ አማራጭ ምንድነው?
ሮስካ ቤት ፈላጊዎች በቅድሚያ ሀምሳ አምስት ሺህ ብር በመክፈል አባል የሚሆኑበትና በየወሩ ደግሞ ሁለት ሺህ ብር ዝግ የባንክ አካውንት ቆጥበዉ የዕጣ ባለዕድል ሲሆኑ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት የክፍያ አማራጭ ነዉ፡፡
ይህ የከፍያ አማራጭ በቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ተገምግሞ ዉሳኔ ያልተሰጠበት ቢሆንም ‘በርካታ’ ቤት ፈላጊዎች ክፍያ እየፈጸሙበት ይገኛል።
ሮስካ ‘እቁብ ነው፤ ተዘዋዋሪ ፈንድ ነው። በየተራ ነው መኖሪያ ቤት የሚሰራው። እና ይህንን ጀምረን የመጀመሪያ ዙር መደብ እጣ የማዉጣት ስነስርዐት አድርገናል’ ሲሉ አቶ አለማዉ አሁናዊ ሁኔታዉን ያስረዳሉ።
የሮስካ መጀመሪያው ዙር እጣ ጥር 02፣ 2015 ዓም የወጣ ሲሆን “እጣ ካወጣን በኋላ የመሬት ነክ አገልግሎት እንዳይሰጥ በክፍለ ከተማዉ ታግዶ ወደ 4 ወር ስለቆየ እሱም ትንሽ ወደ ስራ እንዳንገባ መንገራገጭ ፈጥሯል” ብለዋል።
አሁን ላይ የመጀመሪያ ዙር ባለ እጣዎችን ሁለት ሳይቶች ላይ የማደራጀት ስራ መጀመራቸዉንም ተናግረዋል።
ከጥር 02 በኋላ ለምን እጣ አልወጣም ለሚለዉ ጥያቄ ሲመልሱም “የመጀመሪያዉን እጣ አዉጥተን (የመሬት አገልግሎት) ለ 4 ወር ተዘጋ። አራት ወር መጠበቅ ነበረብን። ሁለተኛ ዙር ለመሄድ የመጀመሪያዉን ማስኬድ አለብን። ምክንያቱም ገንዘቡን ወጪ የምናደርገዉ ከቋት ወይም ከተጠራቀምዉ ፈንድ ላይ ስለሆነ አንድ ላይ መደራረብ አይችልም” ብለዋል።
ሁለተኛዉን ዙር እጣ የማዉጣት ሂደትም በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም አቶ አለማዉ ተናግረዋል።
መደበኛ ሞዴልን በተመለከተ
ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግን በመደበኛው ሞዴል እስካሁን ስምንት ማህበራትን ማደራጀቱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪ ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኢንጂነር መኮንን ሚጀናም “ጎጆ ብሪጅ አሁን ወደ ስምንት ሳይት ነው ይዞ ያለዉ። በነዚህ ስምንት ሳይቶች/ብሎኮች ላይ 1005 ሰዎች ናቸዉ የተደራጁት” ብለዋል።
“ከቤቶች አላማ ጋር ተዛማጅ የሆነ ስራ እየሰራ ስለሆነ አብሮን ለማልማት እንደ ፓይለት ፕሮጀክት ነው አብረን የጀመርነዉ” ያሉት ኢ/ር መኮንን “ዉጤታማ መሆኑን እየገመገምን ነው በሂደት የምንለቀዉ እንጂ ብዙ አከባቢ ላይ በጣም በገፍ እንዲገባበት አንፈቅድም። በሂደት ነው ቼክ እያደረግን ውጤታማ እየሆነ ሲሄድ መግባቢያ ሰነዱን እያሻሻልን የምንሄደዉ” ሲሉም ስለ መደበኛው ሞዴል ነግረዉናል።
እነዚህ ስምንት ሳይቶች ያሉበትን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ቼክ ያስረዱት የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማዉ ጋሪ “ቡልጋሪያ ማዞሪያ አከባቢ ሳይት የሚባለዉ ላይ ለግንባታ የሚያስፈልገዉ ቅድመ ዝግጅት ሁሉ ተጠናቆ፤ ኮንትራክተር/ስራ ተቋራጭ ተመርጦ፤ ዉል ስምምነት ተፈርሞ ስራዉን ጀምሯል” ብለዋል።
ጣልያን ኤምባሲ ሳይት ላይ ደግሞ የስራ ተቋራጭ ኮንትራት ይዘቶች ላይ ከማህበሩ በኩል ጥያቄዎች መነሳታቸዉና ዉይይት ተደርጎ አሁን ላይ የመግባቢያ ሀሳብ ላይ መደረሱን እንዲሁም መስከረም ላይ ወደ ግንባታ መግባት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን ነግረዉናል።
የላንቻ አከባቢ ሳይትን በተመለከተ ማህበሩ ክረምቱን የስራ ተቋራጭ መረጣ ጨርሶ መስከረም 2016 ስራ ለማስጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ጎሮ ሳይት ላይ አምስት ማህበራት መደራጀታቸዉን የሚናገሩት አቶ አለማዉ የእዳ እገዳ ወረቀት ያለመጻፉ እና የተለያዩ እክሎች መግጠማቸዉንና የማህበራቱ አባላት እየተጉላሉ መሆኑን እንዲሁም ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገሩና ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ነግረዉናል።
እንደ አጠቃላይ የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ የቤቶች ልማት ስራ በአንድ አመት መጓተቱን የሚናገሩት አቶ አለማዉ “አንዱ ምክንያት መሬት ነክ አገልግሎት አንዳይሰጥ ሁለት ጊዜ መታገዱ ነው። ለዚህ ነው የዘገየው እንጂ እንደ ጎጆ ብሪጅ ፍላጎት ይሄኔ አንዱ ፍጻሜ ላይ ደርሷል ማለት ይቻል ነበር” ብለዋል።
ከጤና ሚኒስቴር እና ዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር የጤና ባለሙያዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ላይ እየሰሩ እንደሆነም የተናገሩ ሲሆን ጤና ሚኒስቴርም መረጃዉን በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ አጋርቶ ነበር፡ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid02PnHVv2sH6DiS4B6m3H72FzPTVitoq2k2GBKEcPQyytBMPkZfZFDFctwHqBTWjB9El&id=100064567187444&mibextid=qC1gEa
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
