ኢትዮ ቴሌኮም የጥሪ ማዕከሉን ዘግቶ ሰራተኞቹን አባሯል?

ethiotelecom refutes claims about the shutting down of its customer service call centres and firing the team ኢትዮ ቴሌኮም

ሰኔ 12፣ 2015

ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች አገልግሎት ጥሪ ማዕከሉን በማቆም ሰራተኞቹ ማባረሩን የሚገልጹ መረጃዎች እየተሰራጩ ነው። በትዊተር ከ13 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አዲስኢንሳይት (AddisInsight) የተባለ የመረጃ ምንጭ ባሰራጨው መረጃ ኢትዮ ቴሌኮም የጥሪ ማእከል አገልግሎት በማቆሙ ምክንያት ከአሁን በኋላ  አገልግሎቱ በኢሜይል፣ በጽሑፍ እና ‘በቻት’ ብቻ የሚሰጥ እንደሚሆን ይጠቅሳል።

በተጨማሪም “በጥሪ ማእከል አገልግሎት ላይ የተሰማራው ቡድን በሙሉ ከስራ መባረሩ ታውቋል” ሲል መረጃውን አጋርቷል። ይህ መረጃ አሁን ላይ ሌሎች 19 ተጠቃሚዎች መልሶ ሲያጋሩት ከ100 በላይ መውደድ አግኝቷል።

ይሁን እንጂ ኢትዮ ቴሌኮም የጥሪ ማእከል አገልግሎቱን እንዳልዘጋ በመግለጽ መረጃው የተሳሳተ መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

“የተባለው ነገር በተሳሳተ መልኩ የመጣ መረጃ ነው። ለጨዋታና ለቧልት የሚደውል ሰው አለ። እነዚህ አይነት ነገሮች የመቆጣጠር ስራዎችን ነው የሰራነው እንጂ የጥሪ ማእከሎቹ የመዝጋት ጥረት ሆነ እንቅስቀሴ የለም። ሰራተኛ የመቀነስ እንቅስቃሴም የለንም” ሲል የድርጅቱ ዋና የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ያስረዳል።

ወደ ጥሪ ማእከሉ በየቀኑ ከ350 ሺህ እስከ 400 ሺህ ጥሪዎች እንደሚመጡ የሚገልጸው አቶ መሳይ ይህም በሰራተኞቹ ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዳለ ሆኖ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመን ዲጂታል ወደሆነው ስርአት የማሸጋገር ስራዎች እየሰራ ነው ብሏል።

“ወደ ጥሪ ማእከል አገልግሎት የሚመጡ ጥሪዎች በጣም እየጨመሩ ነው፣ በየጊዜው እኛ ጋር የሚመጡ ጥሪዎች በጣም ጊዜ የሚያባክኑ፣ አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ ሰዎች በራሳቸው መንገድ ሊያገኟቸው የሚችሉ የጥሪ አይነቶች ይሆናሉ። በዚህ ምክንያት መሰረታዊ አገልግሎት ለማግኘት ለሚደውል ሰው መጨናነቅ ይፈጥራሉ” ሲል ሊትዮጵያ ቼክ ገልጿል።

‘አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ እያደረግነው ነው’

ኢትዮ ቴሌኮም በጥሪ ማእከሎች የሚሰጡ አገልግሎቶች እንደተጠበቀ ሆኖ ዲጂታል ወደ ሆነው ስርአት ማሸጋገር እንደጀመረ ይገልጻል።

ይሄም ከስድስት ወር በፊት ይፋ ማድረጉን በመግለጽ አንድ ደንበኛ በራሱ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችሉት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዙ አርዲ የተሰኙ ‘ቻት ቦቶች’ ማዘጋጀቱን ይጠቁማል።

ይህም ሰዎች የኢትዮ ቴሌኮም የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችና (ትዊተር፣ ቴሌግራም) ድረገጹን እንዲሁም ዋትሳፕ (+251994000000) በመጠቀም የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘት የሚያስችል አሰራር ነው።

“ቀሪ ሂሳቡን ለመጠየቅ፣ የደወላቸው ስልኮች ሊጠይቅ፣ ስልኮች ለማዘጋት የሚደውል አለ። እነዚህ ግን በቀላሉ በራሱ መንገድ ሊሰራቸው የሚችላቸው ናቸው። ስለዚህ በፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ቴሌግራም፥ ኢሜይል መልእክት በመላክ መረጃዎች ማግኘት የሚችልበት አግልግሎት እንዲያገኝ ተደርጓል” ይላል የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ።

በተጨማሪም በ8994፣ በ126 አጭር መልእክት በመላክ የተለያዩ አገልግሎቶች ማግኘት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከ50.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ይገልጻል። ኩባንያው አሉኝ ከሚላቸው ከ50.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች መካከል ከ48 .9 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ ቼክ ከዚህም በተጨማሪ ከሌላ የድርጅቱ ሰራተኛ ማረጋገጥ እንደቻለው የጥሪ ማዕከላት ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች አሁንም በስራቸው ላይ ይገኛሉ፣ ወደፊት ግን የስራ መደብ ሽግሽግ ሊኖር እንደሚችል ጠቁሟል።

ስለዚህ ኢትዮ ቴሌኮም የጥሪ ማዕከሉን ዘግቶ ሰራተኞቹን አባሯል በሚል የተሰራጨው መረጃ ተጋኖ የቀረበ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::