በድብቅ የተሸጡ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦች አሉ?

misleading information claiming the covert sale of Bahir Dar and Hawassa ships

ሰኔ 10፣ 2015

ባሕርዳር እና ሀዋሳ የተሰኙ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦች ‘በድብቅ ተሸጡ’ የሚል መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል።

አንዳንድ በማህበራዊ ትስስር ተጠቃሚዎች ለመርከቦቹ መሸጥ ምክንያት የሆነዉ የውጭ ምዛሪ እጥረት እንደሆነ ሲጠቅሱ ሌሎች ምክንያቶችን እየጻፉ መረጃዉን ያጋሩም አሉ።

ከነዚህ መረጃዎች ጋር መርከቦችን በተመለከተ ዘገባዎችን እና ትንታኔዎችን በመስራት የሚታወቀዉ ትሬድ ዊንድስ (TradeWinds) የተሰኘው ድረ-ገጽ አኤአ ታህሳስ 13፣ 2022 ያጋራዉ መረጃ (https://www.tradewindsnews.com/tankers/stamford-shipping-buying-two-mr2-tankers-from-ethiopian-shipping/2-1-1371682) ስክሪን ቅጂ አብሮ ሲጋራም ተመልክተናል፡

ኢትዮጵያ ቼክ ባሕርዳር እና ሀዋሳ የተሰኙ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦችን በተመለከተ ከዚህ በፊት የተጋሩ የሚዲያ ዘገባዎች፤ የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ማብራሪያ እና ሌሎች መረጃዎችን ቃኝቷል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ (ኢባትሎ) መረጃ እንደሚያመለክተዉ ባሕርዳር እና ሀዋሳ የተባሉት ሁለት መርከቦች የፈሳሽ ጭነት አጓጓዥ መርከቦች ሲሆኑ፣ በዓይነታቸውም ከምርት አጓጓዥ መርከቦች /Product Carriers/ የሚመደቡ ናቸው።

የምርት አጓጓዥ መርከቦች /Product Carriers/ የተጣሩ ማለትም እንደ ቤንዚን፣ ናፍታ፣ ኬሮሲን እና የናፍታ ዘይት የመሳሰሉ የፔትሮሊየም ምርቶችን የሚጭኑና የሚያጓጉዙ መሆናቸዉም የኢባትሎ መረጃ ያሳያል: https://www.facebook.com/ethiopian.esl/posts/pfbid0ETUYZU7z3MwXzNCEfxqzBqsKtL6wMCbbZZErg9UtZQW7vmLyWBa9mqVUDQN2a3K2l

የነዚህ ሁለት መርከቦች ጉዳይ ከወራት በፊት ጀምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘገብ የቆየ መሆኑን የተመለከትን ሲሆን ጉዳዩ ግን ከየትኛዉም ጊዜ በላይ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሽፋን ያገኘዉ ባለፉት ሁለት ቀናት ዉስጥ ነው።

መርከቦቹ በድብቅ ተሸጡ እና የተሸጡትም በዉጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ነው የሚሉት ደግሞ ዋንኞቹ የሚጋሩ መረጃዎች ይዘት ናቸው።

ጉዳዩን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ቼክ ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ደምሰዉ በንቲ ‘መርከቦቹ በዉጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተሸጡ’ የሚለዉ “ፈጽሞ ስህተት ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም መርከቦቹን የመለወጥ ሂደት እንደሚባለው በድብቅ የተካሄደ እንዳልሆነም ነግረዉናል።

“ሂደቱ በግልጽ ነው የተከናወነው። ሂደቱ በቦርድ ታይቶ በቦርድ እዉቅና የተከናወነ ነው። ምንም የአካሄድም ስህተት የለዉም። የድርጅቱን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ነዉ የተነናወነዉ” ብለዋል።

ጉዳዩን “ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ ነገር ይታያል። ይሄ የሀገር ሀብት ነው። ልክ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኩሪያ የሆነ ድርጅት ነው። ይሄ ማለት ምንም አይነት ችግር ቢኖር አይነገር ማለት አይደለም” ያሉት አቶ ደምሰዉ ነገር ግን የሚሰራጩ መረጃዎች ሚዛናዊነታቸዉን የጠበቁ መሆን እንዳለባቸዉ ተናግረዋል።

የሚዲያዎች ምን ዘግበዉ ነበር?

ባሕርዳር እና ሀዋሳ የተሰኙ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦች ጉዳይ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አመራሮችን አስተያየት በመጨመር በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሲዘገብ የቆየ መሆኑ ኢትዮጵያ ቼክ ማረጋገጥ ችሏል።

ለአብነትም ሪፖርተር ጋዜጣ አኤአ ታህሳስ 17፣ 2022 በእንግሊዘኛ ቋንቋ በድረ-ገጹ ባጋራዉ መረጃ ኢባትሎ ሁለቱን መርከቦች በሌላ ሁለገብ የጭነት መርከብ ለመቀየር ያደረገዉ ጥረት ባለመሳካቱ መርከቦቹን ለመሸጥ ማሰቡን ዘግቦ ነበር።

ሁለቱ መርከቦች ሀገሪቱ የምትገዛዉን ነዳጅ እንዲያጓጉዙ ታስቦ የተገዙ መሆናቸዉን፤ ነገር ግን ነዳጅ ሻጮች የሸጡትን ነዳጅ እራሳቸዉ የሚያጓጉዙ በመሆኑ ሁለቱ መርከቦች የታለመላቸዉን አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉም በዘገባዉ ተጠቅሷል።

ይህም ሁለቱን መርከቦች በሌላ ሁለገብ የጭነት መርከብ ለመቀየር ካልሆነም ለመሸጥ ለመወሰኑ ምክንያት እንደሆነ በሪፖርተር ዘገባ ተካቷል፡ https://www.thereporterethiopia.com/28660/

በሌላ በኩል ካፒታል ጋዜጣ አኤአ ታህሳስ 20፣ 2022 በፌስቡክ ገጹ ባጋራዉ መረጃ “አትራፊ ያልሆኑትን ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦቼን በሌላ የደረቅ ጭነት ጫኝ ለመቀየር እየሰራው ነው ሲል የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) አስታወቀ” ሲል ስለ ሁለቱ መርከቦች ዘግቧል።

ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን የማስተዳደር እና የማንቀሳቀስ ልምድ ባለመኖሩ በመጀመሪያ መርከቦቹ ለኢትዮጵያ ነዳጅ ለሚያቀርብ የኩዌት ድርጅት የተላለፉ መሆኑን፤ በመቀጠልም መሰረቱን ዱባይ ያደረገ የመርከብ አስተዳዳሪ እንዲሰራባቸው ተላልፈው እንደነበርና ሆኖም ትርፋማ እንዳልነበሩ በወቅቱ የኢባትሎ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳን ዋቢ አድርጎ ካፒታል ጋዜጣ ጽፏል፡፡

በተጨማሪም መርከቦቹ ሲገዙ የተሰጠ ብድር በ2014 በጀት አመት ተከፍሎ በመጠናቀቁ መርከቦቹን በሌላ አዋጭ እና ሀገሪቱ ልምድ ባላት የደረቅ ብትን ጭነት የመቀየር ሂደት መጀመሩን፤ በሂደቱም የሲንጋፖሩ ስታንፎርድ የተባለ አገናኝ ድርጅት እየሰራ መሆኑን እና የቅየራ ሂደቱም በ6 ወራት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋም ዘግቦ ነበር፡ https://www.facebook.com/capitalethiopia/posts/pfbid02PgVgtMJpXbPUyed9Hypcfh4of42MKsRFuiHVta1tunQWCZChNyR7M2Nv2kBnBrqYl

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በነዚህ ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የቀየራት ግዙፏ ሁለገብ የጭነት መርከብ በመጪው ሰኔ 17 ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የወደብ ማዕከል፣ ጅቡቲ መህልቋን እንደምትጥል  ካፒታል ጋዜጣን ጠቅሶ ትላንት ሰኔ 09፣ 2015 በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ መረጃ አጋርቷል፡ https://www.facebook.com/ethiopian.esl/posts/pfbid02FRwHSG4QR5BrtpuCUFrqwxxwrkhseM2fxKWrp35aZBJDktQUhZjBfz7NwbkL5F9ul

አባይ 2 የሚል ስያሜ የተሰጣት ይህች መርከብ ወደ ስራ ከገባች የ 7 አመት እድሜ ያላት እና በማርሻል አይላንድስ ተመዝግባ በጀርመን የመርከብ አንቀሳቃሽ ድርጅት ስራ ላይ የነበረችው መሆኑም ተጠቅሷል።

ተቋሙ ትላንት ያጋራው ሌላኛዉ መረጃ ደግሞ አዲሷ መርከብ ወደ ስራ ከመግባቷ የድርጅቱን ተጠቃሚነት ያረጋገጠች መሆኑን እና አሁን ስላለችበት ሁኔታ ያትታል።

“አሁን የብረት ምርቶችን ጭኖ ወደ ባልቲክ እያመራ ያለው ይሄው መርከብ የተጣራ ትርፍ ብቻ በቀን 11,000 US dollar ገቢ ለድርጅታችን የሚያስገኝ ሲሆን ለ60 ቀናት በተደረገው የውል ስምምነት መሰረት 660,000 የአሜሪካ ዶላር ያስገኛል ማለት ነው” ይላል መረጃው።

ይህ ስለ ሁለቱ መርከቦች ቅያሬ ሂደትና አዲሷ መርከብ የሚዳስሰዉ መረጃ በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡ https://www.facebook.com/ethiopian.esl/posts/pfbid0UDoUJCscGBtdtsws4poH9CgeLvK12jk8H1XxSPh7D4nbJEByRKfzPEjMSpHewZi6l

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቼክ አባይ 2 በተሰኘችዉ መርከብ ላይ የሚገኘዉ የመርከቦች መለያ ቁጥር (IMO 9743239) ላይ ባደረገዉ ማጣራት መርከቧ በእኤአ በ2016 መገንባቷ እና በማርሻል አይላንድስ ተመዝግባ የነበረ መሆኑንና አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተመዘገበች መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል፡ https://www.vesselfinder.com/vessels/details/9743239

ለማጠቃለል፣ እነዚህ ሁሉ የሚድያ ቅኝቶች እንደሚያስረዱት ባሕርዳር እና ሀዋሳ የተሰኙ ሁለት የኢትዮጵያ መርከቦች ‘በድብቅ ተሸጡ’ የሚለ መረጃ አሳሳች መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::