ዶ/ር አርከበ እቁባይ ‘African Pulse’ ለተባለ ሚዲያ ሰጡት ተብሎ በስፋት የተሰራጨው ጽሑፍ እና ቃለ-ምልልስ በሀሰት የተፈበረከ መሆኑ ተረጋገጠ

ግንቦት 17፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/ — የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ የነበሩት ዶ/ር አርከበ እቁባይ “አፍሪካን ፐልስ” (African Pulse) ለተባለ ድረ-ገጽ ሰጡት የተባለው እና በማህበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ያለው ፖለቲካዊ ትንታኔ እና አስተያየት ከእሳቸው ያልወጣ እና በሀሰት የተፈበረከ መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጠዋል።

‘African Pulse’ በተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ “ስትራቴጂካዊ ራስን ማጥፋት – ዶ/ር አርከበ እቁባይ የህወሓትን አመራር አምርረው ተቹ” በሚል ርዕስ የተጻፈ ጽሑፍ በዛሬው ዕለት ወጥቷል።

ይህ የፈጠራ ጽሑፍ ዶ/ር አርከበን በማስመሰል በርካታ ከባድ የፖለቲካ ትችቶችን የቀድሞ ድርጅታቸው ህወሓት ላይ እንደሰነዘሩ አድርጎ ያቀርባል።

ጽሑፉን ይበልጥ እውነተኛ ለማስመሰልም ዶ/ር አርከበ ስለ ጦርነቱ አጀማመር፣ ስለ ፖለቲካዊ ስህተቶች እና ስለ ድርጅቱ መጻኢ ዕጣ ፈንታ ተናግረዋል ያላቸውን የሀሰት ሀሳቦች አካቷል።

በዚህም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው በስትራቴጂካዊ ድክመት እና በፖለቲካዊ እልህ ውስጥ ወድቀው የትግራይን ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ እንደጣሉ እና ጦርነቱ የተጀመረው በስሜት እንጂ በፖለቲካዊ ስሌት እና በበቂ ዝግጅት እንዳልነበረ በጽሑፉ ላይ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም አመራሩ የፌደራል መንግስቱን እና የሌሎች ኃይሎችን ጥምረት መገመት አለመቻሉን እንደተቹ፣ እንዲሁም የድርጅቱ አመራሮች ለለውጥ ዝግጁ እንዳልሆኑ እና አሁን ባለበት የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ውድቀት ውስጥ ሆኖ ዳግም ስለ ጦርነት ማሰብ የድርጅቱን ህልውና ሙሉ በሙሉ የሚያጠፋ እንደሆነ አድርጎ አስነብቧል።

ይህ ዶ/ር አርከበ ሰጡት የተባለው የፈጠራ ጽሑፍ በዋናነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከታዮች ባፈሩ የፌስቡክ ገጾች እና ግለሰቦች አማካኝነት በስፋት ተጋርቷል።

ከእነዚህም መካከል ወደ 186 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮች ያሉት ጄዚራ አፍሪካ የተባለ ገፅ ይህንኑ ሀሰተኛ መረጃ አጋርቷል።

በተመሳሳይ ከ91 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ቬነስ ዜና የተሰኘ የፌስቡክ ገፅ ጽሑፉን ያሰራጨ ሲሆን ከ33 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት Nebyat Alemu የተባለ ገፅም ይህንኑ መረጃ ተቀብሎ ለተከታዮቹ አጋርቷል።

እነዚህ ገጾች በአጠቃላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው በመሆኑ ይህ ሀሰተኛ መረጃ ብዙሃን ዘንድ እንዲደርስ እና በአንባቢዎች ዘንድ ከፍተኛ ብዥታ እንዲፈጥር ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ቼክ ይህ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ የጉዳዩን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በቀጥታ ዶ/ር አርከበ እቁባይን ጠይቋል።

በማጣራቱም ዶ/ር አርከበ ‘African Pulse.org‘ ለሚባለው ድረ-ገጽ ምንም ዓይነት ቃለ-ምልልስም ሆነ የጽሑፍ አስተያየት አለመስጠታቸውን አረጋግጠዋል።

ዶ/ር አርከበ ለኢትዮጵያ ቼክ በላኩት ቀጥተኛ ምላሽ ላይ ለ Pulse.org ቃለ-ምልልስ ሰጥተው እንደሆነ ተጠይቀው እንደነበር ገልጸው ምንም አይነት ቃለ-ምልልስ አለመስጠታቸውን አስረግጠው ተናግረዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ ሰዎችን እና የፖለቲካ ሰዎችን ስም በመጠቀም ያልተናገሩትን እንደተናገሩ አድርጎ ማሰራጨት የተለመደ የሀሰተኛ መረጃ ስልት ነው።

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንደዚህ አይነት አጠራጣሪ እና የፖለቲካ ትኩሳት ያላቸውን መረጃዎች ሲያነቡ መረጃው የወጣበትን ድረ-ገጽ ታማኝነት እንዲያረጋግጡ እና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከማጋራት እንዲቆጠቡ እንመክራለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::