አንድ የወደቀን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ድሮን ያሳያል በሚል እየተጋራ የሚገኝ ምስል በሰው-ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰራ ነው

መስከረም 13፣ 2019

/ኢትዮጵያ ቼክ/- አንድ የወደቀን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ድሮን ያሳያል የተባል ምስል በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተዘዋወረ እንደሚገኝ ተመልክተናል። በምስሉ ‘የኢትዮጵያ አየር ኃይል ETHIOPIAN AIR FORCE’ የሚል ጽሁፍ ያለበት ድሮን ኮረብታማ አካባቢ ወድቆ ይታያል።

ከበስተኋላው ደግሞ ሚሊተሪ እና ሲቪል ልብስ የለበሱ ግለሰቦች እየጨሰ ወደሚገኘው ድሮን ሲራመዱ ይታያሉ።

ይህን ምስል ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘Zelalem Hailu (One Amhara fano)’ የሚል ስም እና ከ20 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ገጽ ይገኝበታል።

ገጹ “አንድ በሉ!….” ከሚል ጽሁፍ ጋር ምስሉን ያጋራ ሲሆን ልጥፉ በርከት ያሉ አስተያየቶች ተሰጥተውበታል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሉ በሰው-ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰራ መሆኑን አረጋግጧል።

የጉግል ምርት የሆነውንና በሰው-ሰራሽ አስተውሎት የተሰሩ ምስሎች፤ ቪዲዮ እና ድምጾችን ለመለየት የሚረዳው ሲንት አይዲ ዲቴክተርን በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሉ በከፍተኛ እርግጠኛነት (very high confidence) በሰው-ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ መሆኑን ተመልክተናል።

በሰው-ሰራሽ አስተውሎት ተፈብርከው ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እየታዩ ሲሆን በርካቶችን ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሲዳርጉም ይስተዋላል።

በመሆኑም በማህመራዊ ትስስር ገጾች የሚጋሩ አጠራጣሪ የሆኑና ትክክለኛነታቸው ያልተረጋገጠ ምስሎችን ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::