ኢትዮጵያ በ2026 ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ‘ከፍተኛ የተባለውን’ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ IMF አስታውቋል?

ጥቅምት 8፣ 2019

/ኢትዮጵያ ቼክ/- ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እኤአ የ2026 እና 2027 ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ።

ከነዚህ መካከልም “IMF ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተባለውን 9.2% የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምታስመዘግብ አስታውቋል” የሚል ይገኝበታል።

ይህ መረጃ ‘ኮፒ እና ፔስት’ በተደረገ መልኩ በበርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋራ እንደሚገኝም ተመልክተናል።

ይህን መረጃ ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ከ280 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Hana Abiy Ahmed’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል። በዚህ ገጽ የተጋራውን መረጃ ከ50 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው አጋርተውታል።

በተመሳሳይ መልኩ ‘Getnet Almaw Tiruneh’ የሚል ስም እና ከ200 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽም ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከል “ከፍተኛ የተባለውን” የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ IMF’ን ጠቅሶ ጽፏል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በተጋራው መረጃ ላይ ባደረገው ማጣራት መረጃው ሀሰት መሆኑን አረጋግጧል።

እንደ IMF መረጃ እኤአ በ2026 ደቡብ ሱዳን 10.5 % የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስበዘግብ የተተነበየ ሲሆን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት መካከልም በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡ https://web.facebook.com/share/p/1W7tf4cWRP/

በመቀጠልም ኢትዮጵያ በ9.2% ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስተቀመጥ ሩዋንዳ እና ጊኒ በ7.4% እና 7.2% በቅደም ተከተል ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የ2027 (እኤአ) ትንበያን በተመለከተ ደግሞ ኡጋንዳ በ9.9% የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ኢትዮጵያ እና ጊኒ ደግሞ በተመሳሳይ በ7.8% ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በሌላ በኩል ይህ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ በተጋነነ መልኩ እየተጋራ እንደሚገኝም ተመልክተናል።

በጉዳዩ ላይ ዘገባ የሰራው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) የ2026 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ትንበያ (9.2%) “ከሰሃራ በታች አፍሪካ አጠቃላይ አማካይ የዕድገት ትንበያ (4.5 በመቶ) በበርካታ እጥፍ የላቀ መሆኑ ተረጋግጧል” ሲል በፌስቡክ ገጹ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ የ2026 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ትንበያ (9.2%) ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ አማካይ የእድገት ትንበያ (4.5%) ጋር ሲነጻጸር 2.04 እጥፍ ነው።

ስለዚህም “በበርካታ እጥፍ የላቀ መሆኑ ተረጋግጧል” በማለት የቀረበው አገላለጽ ካለው ሃቅ አንጻር ተጋኖ የቀረበ ነው።

በሌላ በኩል እኤአ በ2025 አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ኬንያ ኢትዮጵያን በመብለጥ ከምስራቅ አፍሪካ ትልቋ ኢኮኖሚ እንደሆነች የIMF መረጃ ያመላከተ ሲሆን ይህ ግን ከፈጣን እድገት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ኢትዯጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ከማድረጓ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::