ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከቦታቸው እንደተነሱ የሚጠቅስና በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋራ የሚገኘው ደብዳቤ ፌዝ አዘል እና ሀሰተኛ ነው

መስከረም 18፣ 2019

/ኢትዮጵያ ቼክ/- በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከቦታቸው መነሳታቸውን የሚገልጽ “ደብዳቤ” በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋራ ይገኛል።

ዛሬ እኤአ መስከረም 28፣ 2026 እንደተጻፈ የተገለጸው ደብዳቤ በጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የተጻፈና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የወጣ እንደሆነ ተመላክቷል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን መልቀቂያ መቀበላቸውም በደብዳቤው ተጠቅሷል።

ይህን ደብዳቤ በሰበር መረጃ መልኩ ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከልም ‘Martin Plaut’ እና ‘Jeff Pearce’ የሚል ስም ያላቸው የኤክስ (የቀድሞ ትዊተር) አካውንቶች ይገኙበታል።

በኢንስቲትዩት ኦፍ ኮመንዌልዝ እስተዲስ ተማራማሪ የሆኑትና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት ማርቲን ፕላውት ደብዳቤው “ሀሰተኛ እንደሆነ ተነግሮኛል። (ደብዳቤውን) አጥፍቸዋለሁ። ይቅርታ” በማለት ደብዳቤውን ከገጻቸው አንስተውታል።

በመጀመሪያ ደብዳቤውን በሰበር መልኩ ካጋራ ከሰዓታት በኋላ በጻፋቸው ልጥፎች ደብዳቤው የስላቅ እንደሆን የጻፈው ጄፍ ፒርስ በበኩሉ የመጀመሪያ ልጥፉን አላነሳም፤ ደብዳቤው ስላቅ መሆኑንም የመጀመሪያ ልጥፉ ላይ መረጃ አልሰጠም።

ኢትዮጵያ ቼክ በበኩሉ በደብዳቤው ላይ ማጣራት ያደረገ ሲሆን ደብዳቤው በርካታ ስላቅ የያዘ እንደሆነ ተመልክቷል።

በሀሰተኛ ደብዳቤው ላይ በግልጽ ከሚታዩ ግድፈቶች መካከል በደብዳቤው ግርጌ ላይ የተቀመጠው አርማ አንዱ ሲሆን ከትክክለኛው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አርማ ጋር ሲተያይ የምስል እና ጽሁፍ ግድፈቶች ይታዩበታል።

በዚሁ መሰረት ትክክለኛው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አርማ ላይ የኮከብ ምስል የሌለ ሲሆን በሀሰተኛው ደብዳቤ ላይ ግን የኮከብ ምስል ተቀምጦ ይገኛል።

በተጨማሪም በትክክለኛው አርማ ላይ “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት” የሚል ጽሁፍ ያለ ሲሆን የሀሰተኛው ደብዳቤ አርማ ግን በርከት ያሉ የጽሁፍ ግድፈቶች እንዳሉት ተመልክተናል።

በሌላ በኩል ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከቦታቸው መነሳት በተመለከተ በተረጋገጡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትም ሆነ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጋራ መረጃ የለም፤ ለመንግስት ቅርብ በሆኑ መገናኛ ብዙኃንም አልተዘገበም።

ምንጫቸው የማይታወቅና ተመሳስለው የሚዘጋጁ ደብዳቤዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::