ሰሞኑን በሻምቡ ከተማ ‘ለመንግስት እጃቸውን የሰጡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ያሳያሉ’ በሚል እየተሰራጩ ያሉ ምስሎች የቆዩ ናቸው

ነሐሴ 21፣ 2018

ሰሞኑን በሻምቡ ከተማ ‘ለመንግስት እጃቸውን የሰጡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ያሳያሉ’ በሚል እየተሰራጩ ያሉ ምስሎች የቆዩ ናቸው
/ኢትዮጵያ ቼክ/- ከሰሞኑ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ ለመንግስት እጃቸውን የሰጡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ያሳያሉ በሚል በርከት ያሉ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ይህን መረጃ በሰበር ዜና መልኩ ካሰራጩ የፌስቡክ ገጾች መካከል ‘Ethiopian Green Legacy’ የሚል ስም እና ከ27 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ገጽ ይገኝበታል።
ገጹ “የጠላት ካምፕ መፍረሱን ቀጥሏል። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ የኦነግ ሼኔ (WBO) አባላት በጃል ያዴሳ የሚመሩት ሙሉ ትጥቃቸውን በመያዝ በሰላማዊ መንገድ ለወታደራዊ መንግስት እጃቸውን ሰጥተዋል” የሚል ጽሁፍም ከምስሎቹ ጋር አጋርቷል።
በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች በርከት ያሉ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶችም ይህን መረጃ ያጋሩ ሲሆን አንዳንዶቹ እጃቸውን የሰጡ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ቁጥር 200 እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ ምስሎቹን በምልሰት በመፈለግ ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ ሰሞኑን የተነሱ እንዳልሆኑ አረጋግጧል።
በዚሁ መሰረት ምስሎቹ የዛሬ ዓመት አከባቢ (እኤአ መስከረም 29፣ 2025) በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጋሩ ሲሆኑ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጃ ጃርቴ ወረዳ “በሰላም የገቡ” የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን እንደሚያሳዩ ተዘግቦ ነበር።
በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ዘገባ ከሰሩ መገናኛ ብዙሃን መካከል EBC አንዱ ሲሆን 73 የታጣቂ ቡድኑ አባላት “እጅ ሰጥተዋል” ሲል ዘግቦ ነበር፡ https://www.facebook.com/share/1Hiz34qqM7/?mibextid=wwXIfr
የቆዩና ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::