በመአረግ አማረ ስም ስለተከፈተ ሀሰተኛ የፌስቡክ ገፅ የወጣ ማሳሰቢያ

ነሐሴ 14፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- በማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎው በሚታወቀው በመአረግ አማረ ስም እና ምስል የተከፈተ አንድ የፌስቡክ ገፅ የተለያዩ መረጃዎችን እያጋራ መሆኑን ተመልክተናል።
ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ማጣራት ከ15 ሺህ በላይ ተከታታዮች ያሉት ገፁ ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል። መአረግ ትክክለኛ የፌስቡክ ገፁ ከ152 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ይህ አካውንት ብቻ መሆኑን ለኢትዮጵያ ቼክ ያረጋገጠ ሲሆን ገፁንም በዚህ ሊንክ ማግኘት ይቻላል፡ https://www.facebook.com/share/1D91gjpkCL/
በታዋቂ ግለሰቦች እና ተቋማት ስም የሚከፈቱ ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር ገፆች በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። እነዚህ አካውንቶች የሰዎችን አሳሳች መረጃ የማሰራጨት፣ የማጭበርበር እና የስም የማጥፋት ድርጊቶችን በቀላሉ ለመፈፀም ስለሚጠቀሙባቸው ከፍተኛ ስጋት ደቅነዋል።
ብዙ ጊዜ እነዚህ ገፆች የህዝብን ትኩረት እና እምነት ለማግኘት የታዋቂ ሰዎችን ማንነት በመስረቅ ያልተረጋገጡ የፖለቲካ እና የብሄር ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን ያሰራጫሉ። በተጨማሪም ከባድ የፋይናንስ ማጭበርበሮችን በማካሄድ የውሸት የእርዳታ ጥሪዎችን በማቅረብ እና ሰዎችን የገንዘብ ወጥመድ ውስጥ በመክተት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያደርሳሉ።
ይህ ድርጊት የእውነተኛ አካውንት ባለቤቶችን መልካም ስምና ዝና ከማበላሸቱ ባሻገር ተከታዮች እውነተኛውን ከሀሰተኛው ለይተው ለማወቅ እንዲቸገሩ በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች ላይ ያለውን እምነት ያጠፋል። ስለሆነም የታዋቂ ግለሰቦችን እና ተቋማትን ስም እንዲሁም ምስል በመጠቀም የሚከፈቱ ሀሰተኛ ገፆች ለእንደነዚህ አይነት አሳሳች አደጋዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ሁልጊዜ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል።
ተጠቃሚዎች ማንኛውንም መረጃ ከማመናቸው እና ከማሰራጨታቸው በፊት የገፁን የሰማያዊ ምልክት (Verification Badge)፣ የተከፈተበትን ጊዜ፣ የፖስቶች ይዘት እና የተከታዮች ብዛት በጥንቃቄ መመርመር አለባቸው።
በተጨማሪም ሀሰተኛ እና ተመሳስለው የሚከፈቱ አካውንቶችን፣ ገፆችን እና ቻናሎችን ለመለየት የሚረዱ ጠቋሚ ምልክቶችን ለመመልከት በኢትዮጵያ ቼክ የተዘጋጀውን ይህን አጭር ቪዲዮ መመልከት ትችላላችሁ፡ https://t.me/ethiopiacheck/1344
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





