በሸረሪና የተማረኩ ‘የህወሓት ኃይሎች እና ጦር መሳሪያዎች’ በሚል እየተሰራጩ የሚገኙት ምስሎች የቆዩ ናቸው

ሀምሌ 27፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- ሰሞኑን በፌደራል ሠራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሸረሪና አካባቢ ግጭት መቀስቀሱ ተሰምቷል። ይህን ግጭት መነሻ በማድረግም በፌደራል ሠራዊት የተማረኩ ‘የትግራይ ኃይሎች’ አባላት እና ጦር መሳሪያዎችን ያሳያሉ በሚል በርከት ያሉ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋሩ ይገኛሉ።
እነዚህን ምስሎች ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች መካከልም ‘አውደ ሀገር’ የሚል ስም እና ከ107 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል።
በዚህ ገጽ የተጋራውን የምስል እና ጽሁፍ መረጃ 19 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው ሲያጋሩት በርከት ያሉ አስተያየቶችም ተሰጥቶበታል።
በተጨማሪም ‘Mimi Jarso’ የሚል ስም እና ከ170 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ ተመሳሳይ መረጃን አጋርቷል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ ሰሞኑን ሸረሪና አከባቢ በተከሰተው ግጭት የተማረኩ የትግራይ ኃይሎች አባላትን እና ጦር መሳሪያዎችን እንደማያሳዩ አረጋግጧል።
ምስልን በምልሰት መፈለጊያ ድረ-ገጾችን በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሎቹ ከወራት በፊት በአማራ ክልል ውስጥ የተነሱ መሆናቸውን አረጋግጠናል።
በዚሁ መሰረት ምስሎቹ እኤአ ታህሳስ 15፣ 2025 “በምስራቅ ደምቢያ እና በቆላድባ ከተማ አካባቢ ታጥቀዉ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂ ሃይሎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ ገቡ” በሚል ርዕስ በአማራ ክልል ፕሬዘዳንት ጽ/ቤት የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ የተጋሩ ናቸው፡ https://www.facebook.com/share/14hssp5abfn/?mibextid=wwXIfr
ስለዚህም ምስሎቹ ከአውድ ውጭ የተጋሩ እና አሳሳች መሆናቸውን አረጋግጠናል።
በተለይ በግጭት ወቅት ከአውድ ውጭ እና አሳሳች በሆነ መልኩ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛና አሳሳች መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማጋራታን እንዲሁም ከማመናችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





