በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ወደቀ ስለተባለው ጄት እየተሰራጩ ያሉ ትክክለኛ እና አሳሳች መረጃዎች

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ወደቀ ስለተባለው ጄት እየተሰራጩ ያሉ ትክክለኛ እና አሳሳች መረጃዎች

ነሐሴ 07፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/- ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦራ ወረዳ ጎራ ለመን ቀበሌ ወደቀ ስለተባለ የጦር ጄት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል።

የጄቱ ስብርባሪ አካል ብቻውን እንዲሁም የታጠቁ ሰዎች በስብርባሪው ላይ ቆመው የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎችም እየተጋሩ ይገኛሉ።

አንዳንዶች የጦር ጄቱ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) ታጣቂዎች ተመቶ መውደቁን በመጥቀስ ምስሎቹን ያጋሩ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ ምስሎቹ እና ቪዲዮዎቹ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰሩ እንደሆኑ የጻፉም አሉ።

በተጨማሪም ምስሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጄትን እንደማያሳይ በመጥቀስ መረጃው ሀሰተኛ እንደሆነ የጻፉም አሉ። ከነዚህ መካከልም ‘Demeke Negassa Kube’ የሚል ስም እና ከ500 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል።

ገጹ “የወያኔ ቋሚ ተላላኪዎች እያሰራጩ ያለው ዜና በፍጹም ውሸት ነው ።ጀግናው አየር ኃይላችን እንደዚህ ጨጨባ (ስብርባሪ) ጄት የለውም።ይህንን ስብርባሪ ለራሣችሁ አውሉት።በመንደር ሽፍታ ቀርቶ በሌላም በቀላሉ የሚመታ ጄት የለውም” ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋሩ ስለሚገኙ ምስሎች እና ቪዲዮ ጽፏል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ እና ቪዲዮ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሎቹም ሆነ ቪዲዮ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም በቅንብር የተሰሩ እንዳልሆኑ አረጋግጧል። በተጨማሪም ምስሎቹ እና ቪዲዮ ከዚህ በፊት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጋርተው እንደማያውቁም ተመልክቷል።

የጦር ጄቱም ኤሮ L-39 አልባትሮስ (Aero L-39 Albatros) በመባል የሚታወቅ ሲሆን የቼክ ሪፐብሊክ ስሪት ነው። ይህ ጄት በስፋት ለስልጠና አገልግሎት የሚውል ሲሆን ለአየር ላይ ውጊያ፤ የመሬት ላይ ኢላማዎችን ለማጥቃት እንዲሁም ለስለላ አገልግሎትም መዋል ይችላል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይልም ይህን ጄት ለስልጠና እንደሚጠቀም ከዚህ በፊት የተጠቀሰ ሲሆን ጄቱ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ በተከበረው የአየር ኃይል 90ኛ አመት ክብረ በዓል ላይ ትርዒት ካሳዩ ጄቶች መካከል አንዱ ነበር።

በእለቱም የተወሰኑ የአየር ኃይሉ L-39 አልባትሮስ ጄቶች ትርዒት ያሳዩ ሲሆን የጄቶቹ ትርዒት EBC በእለቱ ባሰራጨው ቀጥታ ስርጭት ቪዲዮ 1፡03፡00 ጀምሮ ይታያል፡ https://www.youtube.com/live/Ib4t9boBZxg?si=uqGOCD92DKVMGo30

በዚህ የEBC ቪዲዮ ውስጥ 5፡30 ደቂቃ ላይ ደግሞ ጄቶቹ በረድፍ ቆመው ይታያሉ፡ https://youtu.be/969VaWBL9EY?si=cJFbiSKI6zBvBFBg

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ቼክ የተከሰከሰውን ጄት ስብርባሪና በክብረ በዓሉ ላይ ትርዒት ያሳዩ L-39 አልባትሮስ ጄቶችን በማነጻጸርም ተመልክቷል። በዚሁ መሰረት የተከሰከሰው እና በትርዒቱ ላይ የተሳተፉት ጄቶች ተመሳሳይ የቀለም ስብጥር እንዳላቸው አረጋግጧል።

ከነዚህ መካከልም ጄቶቹ ሆድ ስር የሚገኘው ሰማያዊ ቀለም፤ ክንፎቹ ጫፍ ላይ ያሉት ቀይ እና ቢጫ ቀለማት እንዲሁም የጄቶቹ ጅራት ጫፍ ላይ የሚገኘው ቢጫ ቀለም ቅብ ይገኙበታል።

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች እንዲሁም በጄቱ ስብርባሪ ምስል ላይ የሚታየውና ጄቱ እንደወደቀ የተገለጸበት ስፍራ መሬት አቀማመጥ መመሳሰል ጄቱ ከጥርጣሬ በላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።

ይሁን እንጂ ጄቱ ተመቶ ወይስ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው የወደቀው የሚለው ጥያቄ በማስረጃ ያልተመለሰ ሲሆን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስትም ስለ ጉዳዩ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::