አልጀዚራ ስለ ምክክር ጠቅላላ ጉባኤ ሰራው በሚል በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ተቀናብሮ የተሰራጨው ሀሰተኛ ዘገባ

ስለ ምክክር ጠቅላላ ጉባኤ ሰራው በሚል በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ተቀናብሮ የተሰራጨው ሀሰተኛ ዘገባ

ነሐሴ 19፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/- አልጀዚራ የዜና ወኪል ስለ ኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤ ሰራው የተባለ ሀሰተኛ ዘገባ በጽሁፍ እና የቪዲዮ መረጃዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል።

ይህ የተሰራጨው የጽሁፍ እና ቪዲዮ መረጃ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያከናወነችው የጠቅላላ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ የውስጥ አለመግባባቶችን በጠመንጃ ግጭት ሳይሆን በውስጣዊ ውይይት ማስተናገድ እንደምትችል ያሳያል በሚል ተዘግቧል ይላል።

ይህ የተሰራጨው የጽሁፍና የቪዲዮ መረጃ የምክክር ጠቅላላው ጉባኤው ውጤቶች ኢትዮጵያን ለሰላምና አካታች ልማት አቅጣጫ ሊመራት ይችላል ይላል።

ይህን የጽሁፍ እና የቪዲዮ መረጃ በስፋት ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ”Hermen Gashaw” የተባለ ወደ 21 ሺህ ተከታዮች ያሉበት ገፅ ይገኛል። በገጹ የተጋራዉን ይኸንን የጽሁፍ እና የቪዲዮ መረጃ ወደ 208 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው ለሌሎች ያጋሩት ሲሆን 51 የሚሆኑ አስተያየቶች ሰጥተውበታል።

ይህንን ጉዳይ ተከትሎ ኢትዮጵያ ቼክ መረጃውን ለማረጋገጥ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ ቪዲዮው እውነተኛ እንዳልሆነ አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ቼክ የጉግል ምርት የሆነዉን ‘ሲንዝ አይዲ ዲቴክተር’ (SynthID Detector) የተባለውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ በመጠቀም በቪዲዮው ላይ ባደረገዉ ማጣራት የተሰራጨው ፅሁፍ ትክክለኛ የዜና አቅራቢም፣ ዘገባም እንደማያሳይ ደርሶበታል።

በዚሁ የምርመራ ውጤት መሰረት በቪዲዮው ውስጥ የሚታየው ምስልም ሆነ የሚሰማው ድምጽ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ የተቀነባበረ የፈጠራ ውጤት መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።

በቪዲዮው ላይ የ’ዜና አቅራቢው’ ቪዲዮ የሚታየው የከንፈር እንቅስቃሴ፣ የፊት ገጽታ እና የድምጽ ቅንብር አንድን ትክክለኛ ሰው አስመስሎ በኮምፒውተር ፕሮግራም የተሰራ እንጂ በገሃዱ ዓለም የተፈጠረን ዘገባ ክስተትን የሚያንጸባርቅ አይደለም።

በተጨማሪ ቪዲዮው Hermen Gashaw በተባለ የፌስቡክ ገፅ የተጫነ እንጂ በተረጋገጡ አልጀዚራ እንግሊዘኛ ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች ላይ የሌለ መሆኑን አረጋግጠናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ መሰል የዲፕፌክ (Deepfake) ቪዲዮዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ በጣም እየተበራከቱ እና በርካታ ሰዎችን ለተሳሳተ መረጃ እያጋለጡ ይገኛሉ።

አሳሳች መረጃ አሰራጪ አካላት እነዚህን እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም እውነተኛ የሚመስሉ ነገር ግን ፈጽሞ ያልተፈጠሩ ክስተቶችን በመፍጠር ህብረተሰቡን በማሳሳት ላይ ይገኛሉ።

ይህ አይነቱ ቴክኖሎጂ የፖለቲካ ውዥንብር ለመፍጠር፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማራመድ፣ እና የሰዎችን ስነልቦና ለመጉዳት ሆን ተብሎ የሚሰራጭ አደገኛ የሀሰተኛ መረጃ (Disinformation) መሳሪያ ሆኗል።

በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ግለሰቦች ያልተናገሩትን እንደተናገሩ አድርጎ በማቅረብ ህብረተሰቡ የተዛባ መረጃን አምኖ እንዲቀበል ማድረግ የተለመደ የማጭበርበር ስልት ሆኖ ብቅ ብሏል።

ሰዎች እውነተኛ ቪዲዮ እየተመለከቱ እንደሆነ በማሰብ እንዲታለሉ እና የተዛባ መረጃን ለሌሎች በማጋራት በማህበረሰቡ ውስጥ አለመተማመንን መፍጠር የዚህ አይነቱ ተግባር ዋና አላማ ነው።

ስለሆነም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ይህንን እያደገ የመጣውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አደጋ በሚገባ ተገንዝበው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንመክራለን።

ማንኛውም አጠራጣሪ እና ተአማኒ ባልሆኑ የመረጃ ምንጮች ወይም ግለሰቦች የሚጋሩ የምስል እና የቪዲዮ መረጃዎችን ልክ እንዳዩት ከማመናችን እና መልሰን ለሌሎች ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት ማድረግ አለብን።

ቪዲዮዎች ያልተለመደ የዓይን ብልጭታ፣ ከድምጽ ጋር የማይሄድ የከንፈር እንቅስቃሴ ወይም ኢተፈጥሮአዊ የሆነ የቆዳ ገጽታ ካላቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በጥሞና መመርመር ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::