በኤርትራ ሀይሎች ተመትቶ የወደቀን የኢትዮጵያ ድሮን ያሳያል በሚል እየተሰራጨ የሚገኘው ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

መጋቢት 19፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- በርከት ያሉ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች ‘ኤርትራ የኢትዮጵያን ድሮን አፋር ክልል አካባቢ መትታ ጣለች’ የሚል መረጃ እያጋሩ ይገኛሉ።
አካውንቶቹ እና ገጾቹ መረጃዉን በሰበር መልኩ እያሰራጩ የሚገኙ ሲሆን ተመቶ ወደቀ የተባለውን ድሮን ያሳያል ያሉትን ምስልም እያጋሩ ይገኛሉ።
ይህን በጽሁፍ እና ምስል የተደገፈ መረጃ ካጋሩ ገጾች መካከል ‘Esmael Dawed Endrise’ የሚል ስም እና ከ68 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እንዲሁም የትክክለኛ የፌስቡክ ገጽነት ማረጋገጫ (verification) ያለው ይገኝበታል።
ገጹ ከምስሉ በተጨማሪ “በኢትዮ ኤርትራ በአፋር አካባቢ ባለ ድንበር Bayraktar TB2.የተሰኘ የበረራ ቁጥሩ AZf 131 የሆነ ቱርክ ሰራሽ ባይራክተር የሚባል ድሮን ዛሬ ወደ ማምሻዉ ላይ መትታ ጥላለች ተባለ” የሚል መልዕክትም በልጥፉ አስፍሯል።
በዚህ ገጽ የተጋራዉን መረጃም ከ70 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰዉ አጋርተዉታል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገዉ ማጣራት ምስሉ በኤርትራ ተመቶ የወደቀን የኢትዮጵያን ድሮን እንደማያሳይ አረጋግጧል።
የምስሉን ትክክለኛነት ለማጣራት ‘SynthID Detector’ የተሰኘዉን የጉግል ድረ-ገጽ የተጠቀምን ሲሆን ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ እንደሆነ አረጋግጠናል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የሚፈበረኩ መሰል ምስሎች ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እየታየ ሲሆን በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎችን ለተሳሳተ ግንዛቤ ሲያጋልጡም ይታያል።
በመሆኑም ተአማኒ ባልሆኑ የመረጃ ምንጮች የሚሰራጩ አጠራጣሪ መረጃዎችን ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





