ይህ ቪዲዮ በትግራይ ክልል የወደመ የፓፓያ እርሻን አያሳይም

ይህ ቪዲዮ በትግራይ ክልል የወደመ የፓፓያ እርሻን አያሳይም

ሰኔ  3፣ 2016

ከ1,600 በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Mulue G Medhanye’ የሚል ስም የሚጠቀም ማረጋገጫ (verification) ያለው የኤክስ (ትዊተር) አካውንት በትግራይ ክልል የወደመ የፓፓያ እርሻን ያሳያል ያለውን ቪዲዮ ከሶስት ቀን በፊት ማጋራቱን ተመልክተናል።

የተጋራው ቪድዮ ከ54,200 ሺህ በላይ እይታዎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም መልሰው አጋርተውታል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ከላይ የተጠቀሰው አካውንት ያጋራው ቪዲዮ ከሌላ ሀገር የተወሰደ መሆኑን አረጋግጧል።

ይህ ቪዲዮ የተቀረጸው በምስራቃዊ ባንግላዴሽ ሲሌት (Sylhet) በተባለች ከተማ አቅራቢያ ሲሆን ቪዲዮውን ከሳምንት በፊት ያጋራውም ‘Artcelnazmulofficial’  የተባለ የዩቱብ ቻናል ነበር። በዩቱብ ቻናሉ መረጃ መሰረት የፓፓያ እርሻው የወደመው በአካባቢው የተከሰተ ንፋስ የቀላቀለ ውሽንፍርን ተከትሎ ነበር።

ትክክለኛውን ቪዲዮ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል: https://youtube.com/shorts/vqs1LBBFRQ8?si=aBcd3faS4UA5BUvn

በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት በእርሻዎች እና በእርሻ መገልገያ መሳሪያዎች ላይ ውድመት መድረሱን በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።

ይሁንና ከአውድ ውጭ ተወስደው የሚሰራጩ ቪዲዮዎች ለሀሠተኛ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ጥንቃቄና ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::