ይህ ምስል ሰሞኑን በአዲግራት አቅራቢያ እንዲሁም ባድመ አከባቢ የወደሙ ታንኮችን አያሳይም

ህዳር 10 ፣ 2019
/ኢትዮጵያ ቼክ/- በስክሪን ቅጂው ላይ የሚታየውና በአዲግራት አቅራቢያ ወይም ባድመ አካባቢ የወደሙ ታንኮችን እንደሚያሳይ የተገለጸ ምስል ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል።
ምስሉን ከሁለት ቀናት በፊት ያጋራው ‘Digital TDF’ የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ምስሉ የወደሙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታንኮችን እንደሚያሳይ ጠቁሟል።
ገጹ “ከአዲግራት ትንሽ ወጥተው ወደ መቀሌ ሊሸሹ የነበሩ የብልጽግና ታጣቂዎች ከሙሉ ትጥቃቸው ጋር ሙሉ ለሙሉ ተደምስሰዋል” የሚል ጽሁፍ ከምስሉ ጋር አጋርቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ምስሉ ትላንት ለሊት ባድመ አካባቢ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የወደሙ የኤርትራ ሠራዊት ታንኮችን እንደሚያሳይ በመግለጽም እየተጋራ ይገኛል።
ይህን ምስል እና የጽሁፍ መረጃ ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች መካከል ‘Kusse Gelebo’ የሚል አካውንት አንዱ ሲሆን “ባድመን መልሶ ለመቆጣጠር ከትናንት ጀምሮ ያለውን አቅምና ኃይል አሰባስቦ የተንቀሳቀሰው የሻዕቢያ ሠራዊት በጀግናው የኢትዮጵያ አየር ኃይል መብረቃዊ ምትና በስትራቴጂክና ካሚካዚ ድሮኖች ከባድ ውድመት ደርሶበታል፤ አከርካሪው ተሰብሯል” የሚል ጽሁፍ አጋርቷል።
በዚህ አካውንት የተጋራውን መረጃም ከ30 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው አጋርተውታል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ከሰሞኑ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አከባቢ ወይም አዲግራት አቅራቢያ የተነሳ እንዳልሆነ አረጋግጧል።
ምስሉ ከሶስተ አመታት በፊት እኤአ 2023 ከተቀረጸ ቪዲዮ ስክሪን ቅጂ (screenshot) የተወሰደ ሲሆን በሩስያ ጦር የወደሙ የዩክሬን ታንኮች እና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን እንደሚያሳይ በወቅቱ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ተዘግቦ ነበር።
በወቅቱ ጉዳዩን ከዘገቡ የዜና አውታሮች መካከል ሮይተርስ አንዱ ሲሆን ዘገባውም በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡ https://www.reuters.com/world/europe/russia-awards-medals-after-claiming-hits-leopard-tanks-us-bradleys-ukraine-2023-06-11/
ከሌላ ቦታ ተወስደው ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





