በሸዊት ውዳሴ ስም የተከፈቱ ሀሰተኛ የፌስቡክ ገፆች ማሳሰቢያ

ግንቦት 6፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- በመምህር እና የፖለቲካ ተንታኝ ሸዊት ውዳሴ ስም እና ምስል የተከፈቱ በርካታ ሀሰተኛ የፌስቡክ ገጾች መኖራቸውን ደርሰንበታል። እነዚህ ገጾች የግለሰቡን ማንነት በመጠቀም የተለያዩ መረጃዎችን እያጋሩ የሚገኙ ሲሆን አንዳንዶቹም ህዝብን የሚያሳስቱ ይዘቶች እንዳሏቸው ተመልክተናል።
መምህር ሸዊት በሀገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በሚሰጣቸው ትንታኔዎች እና በትምህርት ዘርፍ ባለው ተሳትፎ የሚታወቅ ግለሰብ ነው።
ሸዊት ውዳሴ ለኢትዮጵያ ቼክ እንዳረጋገጠው የእሱ ብቸኛው እና ትክክለኛው የፌስቡክ ገጽ https://www.facebook.com/share/18iYLyc8Yu/ ነው።
ይህ ገጽ በአሁኑ ወቅት ከ72 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን ግለሰቡ ትክክለኛ መረጃዎችን እና የራሱን ሐሳቦች የሚያጋራበት ዋነኛ መድረክ ነው።
ከዚህ ትክክለኛ ገጽ በተጨማሪ ከ5 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት እንዲሁም ሌላ ከ2 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ተመሳሳይ ስም እና ምስል የሚጠቀሙ ገጾች ተለይተዋል። እነዚህ ገጾች የሸዊት ውዳሴ እንዳልሆኑ ተረጋግጧል።
የታዋቂ ግለሰቦችን፣ የመንግስት ባለስልጣናትን ወይም የተቋማትን ስም እና አርማ በመጠቀም የሚከፈቱ ገጾች አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥሩ ይታያል።
ስለሆነም ማንኛውንም መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ከመጋራታችን ወይም ከመቀበላችን በፊት የገጹን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ተገቢ ነው።
ሀሰተኛ እና ተመሳስለው የሚከፈቱ አካውንቶችን፣ ገጾችን እና ቻናሎችን በቀላሉ ለመለየት የሚረዱን ጠቋሚ ምልክቶችን ለማወቅ ኢትዮጵያ ቼክ ያዘጋጀውን አጭር እና አስተማሪ ቪዲዮ በዚህ ሊንክ መመልከት ትችላላችሁ፦ https://t.me/ethiopiacheck/1344
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





