የሳውዲው ‘Al Riyadh’ ጋዜጣ ያወጣው ነው በሚል ተቀናብሮ የተሰራጨው ፅሁፍ እና ምስል ሀሰተኛ ነው

ነሐሴ 27፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/- የሳውዲው Al Riyadh ጋዜጣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድን እግር ሲስሙ ያሳያል የሚል ዜና ሰርቷል በሚል አንድ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተሰራጨ ነው።

ምስሉንና አርእስተ ዜናውን ካጋሩት መሀል ፋሲል የኔአለም ‘Fasil Yenealem’ የተባለ በፌስቡክ ላይ ከ269 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ግለሰብ ይገኛል። በተጨማሪም ኤክስ ላይ ወደ 23ሺህ የሚጠጋ ተከታዮች ያሉት @Joe የሚባል የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ መረጃውን አጋርቷል።

ይሁንና ኢትዮጽያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ምስሉም፣ ዜናውም Al Riyadh ጋዜጣ ላይ እንዳልወጣ አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ቼክ Google Lens የተባለ የድህረ ገፅ መረጃ ማጣሪያ በመጠቀም ባረገው ማጣረት የ Al Riyadh አርእስተ ዜና ርእስ የሚጠቀማቸው የአረብኛ ቃላቶች ልዩ ደማቅ ጥቁር የአረብኛ ፅሁፍ ጥበብ እንደሚጠቀም እና አረንጓዴ ቀለም ያለው የቴምር ዛፍ መለያው እንደሆነ አረጋግጧል: https://www.alriyadh.com/

በተጨማሪም Al Riyadh ጋዜጣ አመተ ምህረቱን የሚያስገባው ከአርእስቱ በታች በግልፅ በአውሮፓውያን አመተ ምህረት አቆጣጠር ተጠቅሞ በአግድም መልክ እንደሚያስቀምጥ ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

በተቃራኒው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እና የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ፕሬዚዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድን ያሳያል የተባለው ምስል የAl Riyadh ጋዜጣ መለያ የሆነውን አረንጓዴ የቴምር ዛፍ ሳይሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬቴስ መለያ የሆነውን የወርቅ ቀለም ያለው መለያ ምስል በጉልህ ይታያል።

በተጨማሪም የAl Riyadh ጋዜጣ ሌላ መለያው የሆነውን አመተ ምህረት አገባብ፣ ፊደልና የአውሮፓውያን አመት አቆጣጠር አያሳይም።

የሰው-ሰራሽ አስተውሎት በመጠቀም የሚፈበረኩ እና ከአውድ ወጭ የሚጋሩ ምስል እና ቪዲዮዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::