የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አማካሪ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ላይ አቋም ወስደዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ ነው

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አማካሪ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ላይ አቋም ወስደዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ ነው

ሀምሌ 24፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/- የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የአረብ አገራት እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቡሎስ አገራቸው በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ላይ የጠነከረ እርምጃ ትወስዳለች ብለው ተናግረዋል ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ መሠረት የሌለውና ሐሰተኛ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል።

ከ193 ሺህ በላይ ተከተዮች ያሉት «ጌትነት አልማው ጥሩነህ» የተባለው የፌስቡክ ገፅ ይህ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ኃላፊ «ፀረ-ኢትዮጵያ አደረጃጀቶች ላይ አሜሪካ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል» በሚል የተሳሳተ መረጃ አጋርቷል።

ይህ የፌስቡክ ገፅ ያሰራጨው መረጃ አሳሳች መሆኑ ሳይታወቅ በበርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መልሶ እንዲሰራጭ እና የህዝብን ትኩረት እንዲስብ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ ቼክ ያደረገው ጥልቅ ማጣራት እንደሚያሳየው ማሳድ ቡሎስ በይፋዊ የኤክስ (X) ገፃቸው ላይ ባጋሩት መግለጫ አሜሪካ የተባለውን ዓይነት እርምጃ ትወስዳለች የሚል ንግግር አላደረጉም።

ማሳድ ቡሎስ በሰጡት ቀጥተኛ ማብራሪያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያተኮረው የአሜሪካ ዲፕሎማሲ «ፀረ-ኢትዮጵያ ጥምረትን ለማጠናከር እየሞከረ ነው» ተብለው በየቦታው የቀረቡት ዘገባዎች ሙሉ በሙሉ ውሸት አሳሳችና ህዝብን የሚያሳስቱ መሆናቸውን በግልጽ አስረድተዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድና የሰፊው ቀይ ባሕር ቀጣና አገሮች ጋር በጋራ የልማት፣ የሰላምና የደህንነት ጉዳዮች ላይ በቅርበትና በትብብር እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ዋነኛ አላማ ተፎካካሪ ጎራዎችን መፍጠር ወይም የቀጣናውን ቅራኔዎች ማጥበቅ ሳይሆን ግጭቶችን በማስቀረት ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሆነ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው «አፍሪካ ሪፖርት» (The Africa Report) የተባለው የዜና ምንጭ በቅርቡ ባወጣው የትንታኔ ዘገባ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ በግብፅ-ሶማሊያ-ኤርትራ ምህዋር በኩል እና በኢትዮጵያ-ሶማሊላንድ-እስራኤል ምህዋር በኩል ባለው አህጉራዊ ፖለቲካዊ ውጥረት መካከል ሊወጠር እንደሚችል አመላክቷል።

ይህ የትንታኔ ዘገባ የቀጣናውን ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚያስረዳ እንጂ ማሳድ ቡሎስ እርምጃ እወስዳለሁ ብለው የተናገሩትን የሚያረጋግጥ አይደለም።

በፖለቲከኞች፣ በዲፕሎማቶች እና በታዋቂ ሰዎች ስም ያልተናገሩትን ንግግር እንደተናገሩ አስመስሎ ማሰራጨት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሰፊ ተቀባይነት ለማግኘት የሚደረግ የተለመደ የሐሰተኛ መረጃ (Disinformation) ስልት ነው።

ስለሆነም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንደዚህ ያሉ አጠራጣሪና የፖለቲካ ትኩሳት ያላቸውን መረጃዎች በሚያነቡበት ጊዜ፣ መረጃው የወጣበትን ድረ-ገፅ ታማኝነትና ትክክለኛነት አስቀድመው እንዲያረጋግጡ እና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከማጋራት እንዲቆጠቡ ይመከራል።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::