እነዚህ ምስሎች ሰሞኑን በምስራቅ ወለጋ ዞን በፋኖ ታጣቂዎች የወደመ የአርሶ አደር ቡና ማሳን አያሳዩም

ነሐሴ 28፣ 2018

/ኢትዮጵያ ቼክ/- ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ በመንግስት ጸጥታ አካላት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መከሰቱ ሲዘገብ ሰንብቷል፣ በግጭቱ ምክንያትም በርካታ ነዋሪዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው እንዲሁ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዞኑ በፋኖ ታጣቂዎች የወደመን የአርሶ አደር ቡና ማሳ ያሳያሉ የተባሉ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋሩ ይገኛሉ።

እነዚህ ከትላንት ረቡዕ ነሀሴ 27፣ 2018 ጀምሮ እየተዘዋወሩ የሚገኙ ምስሎች በርካታ ተከታዮች ባላቸው የፌስቡክ አካውንቶች እና ገጾች ጭምር እየተጋሩ አና በርከት ያሉ መስተጋብሮችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።

ይህን መረጃ ካጋሩ መካከል ‘Alex Taye’ የሚል ስምና ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት አካውንት አንዱ ሲሆን “ይህ የፋኖ ጽንፈኞች ያወደሙት የወለጋ አርሶ አደር ቡና ነው” ከሚል ፍሁፍ ጋር ምስሎቹን አጋርቷል።

በዚህ አካውንት የተጋራውን ልጥፍ ከ300 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው ያጋሩት ሲሆን ከ700 በላይ አስተያየቶች ተሰጥተውበታል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ ከሰሞኑ የተነሱ እንዳልሆኑ አረጋግጧል።

ምስልን በምልሰት በመፈለግ (Reverese image search) ባደረግነው ማጣራት ምስሎቹ ከአመት በፊት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጋርተው የነበሩ እንደሆኑ ተመልክተናል።

በወቅቱ ምስሎቹን ያጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾችም ምስሎቹ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ውስጥ የተነሱ እንደሆኑ በመጥቀስ ነበር ምስሎቹን ያጋሩት፡ https://www.facebook.com/share/p/18N8Jj6eDj/?mibextid=wwXIfr

የቆዩና ከሌላ ቦታ ተወስደው ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::