የመረጃ ምንጮቻቸውን በግልጽ የማይጠቅሱ ሚዲያዎችን ከማመናችን በፊት ልንጠይቃቸው የሚገቡ ነጥቦች

ህዳር 3፣ 2016 ዓ.ም
የአንድን መረጃ ታማኝነት ከሚወስኑት ነገሮች መካከል ምንጩ በዋነኛነት ይቀመጣል።
የመረጃ ምንጩም ስሙ፣ ሃላፊነቱ እንዱሁም ለድርጊቱ ያላው ቅርበት በግልጽ መጠቀስ ይኖርበታል። ይህም መሰረታዊ የጋዜጠኝነት መርህ ነው።
ሆኖም የመረጃ ምንጩ የደህንነት ስጋት ሲኖርበት እንዲሁም የመረጃው መውጣት የሚኖረው ጥቅም ይበልጥ ሲያመዝን ይህ መሰረታዊ መርህ በልዩ ሁኔታ ሊታለፍ ይችላል።
ይህ ሲሆንም የመረጃ ምንጩ ለምን ማንነቱ እንዳልተገልጸ አሳማኝ ማብራሪያ ማቅረብ እንዲሁም የመረጃ ምንጩ ለጉዳዩ ያለውን ቅርበት መግለጽ በጋዜጠኝነት ሙያ የቆየና የተለመደ አሰራር ነው።
ነገር ግን ይህ በልዩ ሁኔታ መታለፍ የሚኖርበት ጥብቅ መርህ በሀገራችን መረጃ አቅራቢዎች በተደጋጋሚ የሚጣስ ብሎም የሁልጊዜ አሰራር እየሆነ መምጣቱን መታዘብ ችለናል።
አሰራሩ በተለየም ዩቱብን መሰረት ባደረጉ መረጃ አቅራቢዎች በስፋት የሚታይ ሲሆን “ምንጮቻችን”፣ “ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ባለስልጣን”፣ “ጉዳዩን የሚከታተሉ ዲፕሎማቶች” ወዘተ የሚሉ ግልጽነትን የሚያዳፍኑ ቃላትንና ሀረጎች ዘወትር ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ።
እንዲህ ያሉ መረጃ አቅራቢዎች ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ቆም ብለን ማሰብና የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ያስፈልጋል፥
- መረጃ አቅራቢው በተደጋጋሚ ስማቸው፣ ሃላፊነታቸውና ለድርጊቱ ያላቸው ቅርበት በግልጽ የተጠቀሱ ምንጮችን ይጠቀማል?
- መረጃ አቅራቢው የምንጮቹን ማንነት መግለጽ ያልፈለገበትን ምክንያት በግልጽ አብራርቷል?
- መረጃ አቅራቢው የምንጩን ማንነት በግልጽ ባይጠቅስም ከመረጃ ምንጩ ያገኛቸውን ዶክመንቶች፣ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች ወይም ሌሎች ማስረጃዎችን አቅርቧል?
- መረጃ አቅራቢው በግልጽ ካልጠቀሰው ምንጭ በተጨማሪ ሌሎች በግልጽ የተጠቀሱ የመረጃ ምንጮን ተጠቅሟል?
ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ያገኘነው ምላሽ በአመዛኙ አሉታዊ ከሆነ መረጃ አቅራቢው ለሀሠተኛና ለተዛቡ መርጃዎች ሊያጋልጠን ስለሚችል ቆም ብለን ማሰብና መረጃ የምናገኝበት አማራጭ ማስተካከል ይጠበቅብናል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
