በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ስደተኞች ላይ ያነጣጠሩ ሀሰተኛ መረጃዎች ጉዳይ እንዳሳሳበዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቀ

ታህሳስ 14፣ 2018
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) በጋምቤላ ክልል ተጠልለዉ የሚገኙ ስደተኞች ላይ በማነጣጠር በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተሰራጩ የሚገኙ ሀሰተኛ መረጃዎች እንዳሳሳበዉ ገለጸ።
ጉዳዩ በአፋጣኝ መፍትሄ ካልተበጀለት በአካባቢዉ ዉጥረትን ሊያባብስ እንደሚችልም ድርጅቱ ዛሬ ታህሳስ 14፤ 2018 ባወጣዉ መግለጫ አሳስቧል።
ከሰሞኑ በጋምቤላ ክልል በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ሲዘገብ ሰንብቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በክልሉ ያለዉ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታና ሁሉም ሰዉ ስደተኞች እና የስደተኞቹ አስተናጋጅ (ተቀባይ) ማህበረሰቦችን ለአደጋ የሚያጋልጡ የጥላቻ ንግግሮችን ከማሰራጨት እንዲታቀቡ ጥሪዉን አቅርቧል።
ስደተኞቹ በሀገራቸው ከገጠማቸው ጥቃት በመሸሽ ደህንነት እና ከለላ ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ የጠቀሰዉ ድርጅቱ በክልሉ ያለዉ ሁኔታ የምግብ አቅርቦት እና ውሀ ስርጭትን ጨምሮ የተወሰኑ አገልግሎቶችን ማስተጓጎሉን ጠቅሷል።
በክልሉ ስላለዉ ሁኔታም በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነና የስደተኞችን፤ አስተናጋጅ ማህበረሰብ እና ሰብዓዊ ሰራተኞችን ደህንነት በተመለከተም ከባለስልጣናት ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።
በሌላ በኩል ድርጅቱ ስደተኞቹን የተመለከቱ ሀሰተኛ መረጃዎች እንዳሳሰቡት ቢገልጽም ስለ መረጃዎቹ ምንነት ወይም ዝርዝር በግልጽ ያለዉ ነገር የለም።
በጋምቤላ ክልል በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን በተርኪዲ መጠለያ ጣቢያ 72 ሺህ፣ በኩሌ የስደተኞች መጠለያ 54 ሺህ እንዲሁም በጉኝየል ስደተኛ መጠለያ 120 ሺህ ስደተኞች እንደሚገኙ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
