በማህበራዊ ሚዲያ በሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ሰለባ ላለመሆን የሚረዱ ነጥቦች

twitter verification

ነሐሴ  13፣ 2016

በማህበራዊ ሚዲያ ከምናያቸው አሉታዊ ክንውኖች መካከል የማጭበርበር ድርጊት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደብ ነው። ብዙ ሰዎችም የዚህ አሉታዊ ድርጊት ሰለባ በመሆን ገንዘባቸውን አጥተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክም ባለፉት አመታት ይህን አሉታዊ ድርጊት የሚያጋልጡ ተከታታይ የማጋለጥ እና የማንቃት ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ሆኖም ድርጊቱ አሁንም ተባብሶ የቀጠለ ስለመሆኑ በሚያደርጋቸው የማህበራዊ ሚዲያ ክትትሎች እንዲሁም ከሚደርሱት ጥቆማዎች ይረዳል።

በማህበራዊ ሚዲያ በሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ላለመታለል ቀዳሚው ተግባር እራስን ማንቃትና ማስተማር ስለመሆኑ የብዙዎች ምክር ነው። ስለሆነም የዚህ አሉታዊ ድርጊት ሰለባ ላለመሆን የሚከተሉትን የጥንቃቄ ነጥቦች እናስተውል:

– ያልተለመዱ ግብዣዎች: ብዙ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት የመጀመሪያ ተግባራቸው ሊያጠቁት ወደፈልጉት ሰው የአብረን እንስራ፣ እንደግ፣ እንጠቀም ወይም እንተባበር የሚል ግብዣ ነው። ግብዣው እንደ ቴሌግራም፣ ዋትስአፕ አልያም ሜሴንጀር በመሰሉ የግል መልዕክት መለዋወጫ ዘዴዎች ሊመጣ ይችላ። እንዲሁም ለሁሉም እንዲደርስ ሆኖ በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ሊጋራ ይችላል። ግብዣው ከማናዎቃቸው ሰዎች ብሎም የድርጅቶችንና የተቋማትን ስም በመጠቀም ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ አጠራጣሪና ያልተለመዱ ግብዣዎች ሲደርሱን ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል።

– የግል መረጃ መጠየቅ: ከላይ የተጠቀሱት ጋባዦች በመቀጠልም የግል መረጃዎችን ሊጠይቁን ይችላሉ። የግል መረጃዎችን ስንል ስማችንን፣ ስልክ ቁጥራችንን፣ የኢሜል አድራሻችንን፣ የባንክ አካውንታችንን ወይም የይለፍ ቃላችንን (ፓስዎርዳችንን) ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ከአጭበርባሪዎች የመሆን እድላቸው የሰፋ ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

– ክፍያ መጠየቅ: የአብረን እንስራና እንደግ ግብዣው ቀጣዩና አደገኛው ደረጃ ክፍያ መጠየቅ ነው። ክፍያዎቹ ለመመዝገቢያ፣ ለአባልነት፣ ለግዥ፣ ለኪራይ፣ ለአገልግሎት ወዘተ በሚሉ አታላይ ቃላቶች የታጀለ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ የገንዘብ ይክፈሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ተገቢውን ጥንቃቄ ማደርግ ይኖርብናል።

– አማላይና የተጋነኑ ገንዘቦች: አጭበርባሪዎች ወደራሳቸው ለመሳብ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል አማላይና በጣም የተጋነኑ ሽልማቶችን፣ ስጦታዎችን፣ ትርፎችን፣ የውጭ አገር ጉዞዎችን እንዲሁም የስራ እድሎችን እንደሚያቀርቡ መናገር ነው። ይህም በሺዎች፣ በመቶ ሺዎች ብሎም በሚሊዮኖች ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ የተጋነኑ ጥሮችንና ዕድሎችን ስናይ እንጠንቀቅ።

– የማያቋርጥ ውትወታ: ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ተጠቂያቸውን ለማሸነፍ የማያቋርጥ ውትወታን መጠቀም የተለመደ ተግባራቸው ነው። ይህም የውስጥ መልዕክት መለዋውጫ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚከወን ሲሆን በጣም ጥሩና አሳቢ ሆነው የመቅረብ ልምድ አላቸው። ተደጋጋሚ ውትወታና ሽንገላ ከበዛብዎት ከአጭበርባሪዎች ሊሆን ስለሚችል ይጠንቀቁ።

– አጠራጣሪ ማስፈንጠሪያዎች: አጭበርባሪዎች ብዙ ጊዜ ማስፈንጠሪያዎችን እንዲከተሉ ግብዣዎችን ያቀርባሉ። እነዚህ ማስፈንጠሪያዎች ወደአልተለመዱ አይነት ድረገጾች ሊያደርሱ ይችላሉ። አልያም የማይከፈቱ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ አጠራጣሪ ማስፈንጠሪያዎችን ከመከተልዎ በፊት ቆም ብለው ያስቡ።

– ግልጽ ያልሆነ ማንነት: አብዛኞቹ አጭበርባሪዎች ስለራሳቸው ማንነት ግለጽ መረጃ አይናገሩም። ማለም ጽማቸውን፣ አድራሻቸውን፣ ድረገጻቸውን ወይም የስራ ፍቃዳቸውን በዝርዝርና በግልጽ አያስቀምጡም። ግልጽ ያልሆነ ማንነት ያላቸው አካላት ግብዣ ሲያቀርቡልን ቆም ብለን ማሰብ ተገቢ ይሆናል።

– ማስመሰል: ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የማጭበርበር ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት የታዋቂ ተቋማትን ስምና አርማ ወይም ማህተምና አድራሻ መጠቀም የተለመደ ተግባራቸው ነው። የነዚህን ተቋማት ስማና አርማ በመጠቀምም የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን መክፈት እንዲሁም ደብዳቤዎችን ማዘጋጀት መለያቸው ነው። እንዲህ ባሉ ተመሳስለው በተከፈቱ ገጾች ወይም በተጻፉ ደብዳቤዎች እንዳይታለሉ ምርመራ ያድርጉ።

በማህበራዊ ሚዲያ በሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ሰለባ ላለመሆን እራሳችንን እራሳችንን እናንቃ፣ እናስተምር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::