ይህ ምስል በቅርቡ ደቡባዊ ትግራይ ላይ ተጠምዶ የሚታይ መድፍን አያሳይም

ጥር 23, 2018

ከሰሞኑ በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መሀል በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ውጥረት እና ግጭት መንገሱን ተከትሎ በርካታ ያልተረጋገጡ እና የተሳሳቱ መረጃዎች ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተሰራጩ ይገኛሉ።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ሰሞኑን የትግራይ ሀይሎች ደቡባዊ ትግራይ ላይ ጠመዱት የተባለ የመድፍ ምስል ይገኝበታል።

መረጃውን ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች መካከል ”Mahari T Hagos” የሚል ስም ያለው እና ከ20 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ይገኝበታል። ገፁ ”ደቡባዊ ትግራይ ጨርጨር ወረዳ የገበሬ ቤት ግቢ ውስጥ ተተክሎ ያለ መድፍ ነው” ብሎ ጠቅሷል።

በዚህ ገፅ የተጋራውን መረጃ 22 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው ያጋሩት ሲሆን 59 የሚሆኑት አስተያየቶች ሰጥተውበታል።

በተመሳሳይ መልኩ ከ6,400 በላይ ተከታዮች ያሉት እና ”Hujira Press” የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገፅም ምስሉን እና መረጃውን አጋርቷል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ሰሞኑን ደቡባዊ ትግራይ ዞን ጨርጨር ወረዳ ላይ የተጠመደ መድፍ እንደማያሳይ አረጋግጧል።

የጉግልን ምስልን በምልሰት መፈለጊያ (Google Reverse Image Search) በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሉ ከአራት አመት በላይ በፊት በማህበራዊ ትስስር ገፆች ተጋርቶ እንደነበር ተመለክተናል።

በወቅቱ የመድፉን ምስል ያጋሩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች የትግራይ ሀይሎች መድፉን ማርከው ሲጠቀሙበት የነበረ እንደሆነ በመጥቀስ ምስሉን አጋርተው ነበር: https://www.facebook.com/share/p/1C4eoJBJq3/ 

ከሌላ ቦታ ተወስደው ከአውድ ውጭ በሆነ መልክ የሚጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ