ይህ ምስል ከሰሞኑ በመከላከያ ሠራዊት የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን አያሳይም

This image does not show weapons captured by the Defense Forces

ነሐሴ 03፣ 2015 ዓ.ም

ይህ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች የሚታዩበት ምስል ሰሞኑን የተነሳ እንደሆነ በሚገልጽ መልኩ በአንዳንድ የፌስቡክ ገጾችና አካውንቶች ሲጋራ ተመልክተናል።

እነዚህ ገጾችና አካውንቶች በምስሉ የሚታዩት የጦር መሳሪያዎች በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በመከላከያ ሠራዊት የተማረኩ እንደሆኑ በሚገልጽ መልኩ መረጃውን እንዳጋሩም ተመልክተናል።

ምስሉን ካጋሩ ገጾች መካከል አንዱ “ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዛሬው ዕለት የተለያዩ ትላልቅ የጦር መሳሪያዎችን ከጃውሳ እጅ በመማረክ ከፍተኛ ድል አስመዝግቧል” የሚል መልዕክትም ከምስሉ ጋር አጋርቷል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ ምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ከሰሞኑ ግጭት ጋር በተገናኘ የተነሳ እንዳልሆነ ማረጋገጥ ችሏል።

ምስሉ እኤአ መስከረም 04፣ 2021 በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ ተጋርቶ እንደነበርም ተመልክተናል፡ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid0ucy3QTGborpwo57iThC8BhhyVp59MaW9ac8Z4LauPKN3kU9MbvRdgxCaFuHa2unal&id=654684251716987&mibextid=qC1gEa

ምስሉ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት በሰሜን ወሎ በኩል ወደ አማራ ክልል ከገቡ የትግራይ ሀይሎች የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን የሚያሳይ እንደሆነም ከመረጃው መረዳት ችለናል።

በሌላ በኩል ሰሞኑን በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በመንግስት ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መከሰቱ ይታወቃል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ከአውድ ውጪ እየቀረቡ ያሉ ምስሎች፣ ቪድዮዎች እና የፅሁፍ መረጃዎች እንዳሉ ተመልክተናል።

እንዲህ አይነት አሳሳች መረጃዎችን ባለማሰራጨት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::