እነዚህ የሳተላይት ምስሎች የኤርትራ ጦር ሰሞኑን የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ እየቆፈረ ያለን አዲስ ምሽግ ያሳያሉ?

እነዚህ የሳተላይት ምስሎች የኤርትራ ጦር ሰሞኑን የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ እየቆፈረ ያለን አዲስ ምሽግ ያሳያሉ?

ነሀሴ 17፣ 2017

በርከት ያሉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የኤርትራ ጦር ሰሞኑን የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ እየቆፈረ ያለውን አዲስ ምሽግ ያሳያሉ ያሏቸውን የሳተላይት ምስሎች እያጋሩ ይገኛሉ።

የፌስቡክ ተጠቃሚዎቹ ምሽጎቹ ቡሬ አከባቢ የተቆፈሩ መሆናቸውን የጠቀሱ ሲሆን አንዳንዶቹ በሰበር ዜና መልኩ ምስሎቹን ማጋራታቸዉን ተመልክተናል።

ይህን መረጃ ካጋሩ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች መካከል ‘Darash Media -ዳራሽ ምድያ ፣ Wasu Mohammed – Mereja እና Kaachaamaalee Koyyee’ የሚል ስም ያላቸው ይገኙበታል።

በነዚህ ገጾች እና አካውንቶች የተጋሩ የፅሁፍ እና የሳተላይት ምስል መረጃዎች በበርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው መጋራታቸውንም ተመልክተናል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በሳተላይት ምስሎቹ ላይ ባደረገዉ ማጣራት ምስሎቹ የኤርትራ ጦር ሰሞኑን በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ እየቆፈረ ያለን አዲስ ምሽግ እንደማያሳዩ አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ ቼክ የመረጃዉን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ጉግል ኤርዝን በመጠቀም የቦታዎቹን ታሪካዊ የሳተላይት ምስል (Google Earth Historical Imagery) ተመልክቷል።

በዚሁ መሰረት “አዲስ የተቆፈረ ምሽግ” በሚል ምልክት ተደርጎባቸው የተጋሩት የመሬት ላይ ግንባታዎች (Structures) ከሰሞኑ የተሰሩ ሳይሆን ለአመታት በቦታው የነበሩ ናቸው።

የጉግል ኤርዝ ‘Historical Imagery’ የአካባቢውን የበርካታ አመታት ታሪካዊ ሳተላይት ምስሎች የሚያሳይ ሲሆን “አዲስ ምሽግ” በሚል የተሰራጩት ግንባታዎችም በትንሹ ከ10 አመታት በላይ በቦታው የነበሩ መሆናቸዉን አረጋግጠናል።

መረጃውን ባሰራጩ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች የተጋሩ አራት የሳተላይት ምስሎች መገኛ (Coordinates) 12°41’33″N 42°15’10″E ፣ 12°41’29″N 42°15’14″E ፣ 12°41’32″N 42°15’11″E እና 12°38’30″N 42°16’48″E ሲሆኑ የቦታዎቹን ታሪካዊ ምስል እነዚህን መገኛ በመጠቀም መመልከት ይቻላል።

ትክክለኛነታቸው ያልተረጋጠ መረጃዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::