ከሰሞኑ ጥያቄን የፈጠረዉና ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጠው የቪፒኤን (VPN) አገልግሎት ምንድን ነው?

ግንቦት 10፣ 2015 ዓ.ም
ከሰሞኑ ኢትዮ ቴሌኮም በሞባይል ቪፒኤን (VPN) አገልግሎቱ ላይ የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉን መግለጹን ተከትሎ በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ዘንድ ጥያቄን አጭሯል።
ተቋሙ የሞባይል ቪፒኤን አገልግሎንት ዋጋ ማሻሻያን በተመለከተ በትዊተር አካዉንቱ ባጋራዉ መረጃ ስር የተለያዩ ግብረ መልሶች ሲጻፉም ተመልክተናል።
ከነዚህ ግብረ መልሶች መካከል በርካቶቹ ተቋሙ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ገደብ ሲጣል ተጠቃሚዎች በስልካቸዉ ወይም ኮምፒተራቸዉ በመጫን የሚጠቀሙበትን ቪፒኤን (VPN) አገልግሎት በክፍያ ማስጠቀም እንደጀመረ በሚመስል በመረዳት አስትያየታቸዉን ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ቼክም ይህን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮ ቴሌኮም ኢንተርፕራይዝ ቢዝነስ ዲፓርትመንት የሴልስ ኢንጂነሪንግ ማናጀር የሆኑትን ኢንጂነር ገዛኸኝ ታፈሰን አናግሯል።
በተለምዶ ቪፒኤን ከሚባለው ጋር “በፍጹም አይገናኝም፤ ይሄኛው ኮኔክሽን ነው” ያሉት ኢንጂነር ገዛኸኝ፤ በተለምዶ ቪፒኤን የሚባለዉ መተግበሪያ ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም ለደንበኖቹ የሚያቀርበው አገልግሎት ግን መተግበሪያ /አፕሊኬሽን/ ሳይሆን ግንኙነት /ኮኔክሽን/ መሆኑን ይገልጻሉ።
አገልግሎቱ አዲስ እንዳልሆነ፤ የተለያዩ ተቋማት ከዚህ በፊትም ሲጠቀሙበት የነበረ እና ‘MPLS VPN’ በመባል የሚያታወቅ መሆኑንም ያስረዳሉ።
“አሁን ያወጣነዉ የዋጋ ቅናሽ ለ ‘MPLS VPN’ አገልግሎት ነው” ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ሁለት አይነት የብሮድባንድ አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቀሱት ኢንጂነሩ አንደኛዉ የኢንተርኔት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ብሮድባንድ ቪፒኤን እንደሆነ ይናገራሉ።
የብሮድባንድ ቪፒኤን የሚባለዉም ኢትዮ ቴሌኮም ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠዉ የዳታ ብቻ ግንኙነት/ኮኔክሽን መሆኑን በዚህም ተቋማቱ የራሳቸዉን ዳታ የሚያገኙበት፤ የሚቀባበሉበት እና ፕሮሰስ የሚያደርጉበት ሲስተም መሆኑንም ይገልጻሉ።
“ድርጅቶች ወይም ተቋማት ባለዉ የፐብሊክ ኔትወርክ መሰረተ ልማት ላይ ዳታ ብቻ ሊያስተላልፉበት የሚችሉበት የራሳቸዉ የግል ኔትወርክ ነው” ብለዋል።
ይህ ኔትወርክ ከኢንተርኔት ዉጭ የሆነ ከቅርንጫፎቻቸዉ ወደ ዳታ ማዕከላቸው ወይም ከዳታ ማዕከላቸው ወደ ዳታ ቅርንጫፎቻቸዉ ደህንነቱ የተጠበቀ ዳታ የሚቀባበሉበት መሆኑንም ገልጸዋል።
“ለምሳሌ ባንኮች የፋይናንስ ሲስተምን ሲያሳልጡ ወይም ቅርንጫፎች ከኮር ባንኪንግ ጋር ሲገናኙ ፒዩር በሆነው ቪፒኤ ወይም የዳታ ኮኔክሽን ነው። ምክንያቱ ደግሞ ኢንተርኔት ሴኪዩር ስላልሆነ ነው። ቪፒኤን ደግሞ በአንጻሩ ሴኪዩር ነው፤ እንደ ኢንተርኔት ወደ አለም አቀፍ የሚወጣ አይደለም” ብለዋል።
በተለምዶ የሚታወቀው ቪፒኤን “በሌላ ሰው ኔትወርክ ተጠቅመህ ኢንተርኔትን ማግኘት ወይም ደግሞ በሌላ ሀገር ጌትዌይ ተጠቅመህ ኢንተርኔትን የማግኘት እድል ነው የሚሰጥህ። ከኢትዮ ቴሌኮም ‘MPLS VPN’ አገልግሎት ጋር ምንም አይገናኝም” ብለዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ተቋሙ የቪፒኤን አገልግሎቶችን በሁለት አማራጭ የሚያቀርብ ሲሆን እነዚህም የሞባይል ብሮድባንድ ቪፒኤን እና የፊክስድ ብሮድባንድ ቪፒኤን ናቸው።
ቪፒኤን (VPN) በኢትዮጵያ
ቪፒኤን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ምህጻረ ቃል ሲሆን ሲተነተን ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርክ (Virtual Private Network) ማለት ነው። በአማርኛም አንዳንድ ባለሙያዎች የግል አውታረ መረብ በማለት ይጠሩታል።
ቪፒኤን በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረጉ የመረጃ ልዉዉጦች ደህንነታቸው እና ሚስጥራዊነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚረዳ መተግበሪያ/አፕሊኬሽን ነው።
ይሁን እንጂ ቪፒኤን የሚለው ቃል በሀገራችን በተለይ ባልፉት አመታት በብዛት የሚጠቀስ እና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ዘንድ ጥቅም ላይ የሚዉል ቢሆንም በአብዛኞች ዘንድ ጥቅም ላይ የሚዉለው ከመረጃ ደህንነት አንጻር ሳይሆን ሰዎች መረጃን ለማግነት ካላቸው ፍላጎት በመነሳት ነው።
በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እና መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ላይ እግድ ሲጣል የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ቪፒኤን በስልኮቻቸዉ ወይም በኮምፒዩተሮቻቸው በመጫን የታገዱትን የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ይዳስሳሉ፤ በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችም መልዕክት ይለዋወጣሉ።
በስልኮቻችን እና ኮምፒዩተሮቻችን ውስጥ የሚገኙ የመተግበሪያዎች ማዉረጃች ዉስጥ በርካታ የቪፒኤን (VPN) አማራጮች ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ክፍያ የሚጠይቁ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ክፍያ የማይጠይቁ ናቸው።
ይሁን እንጂ ቪፒኤን (VPN) የመረጃ ልዉዉጦችን ደህንነት እና ሚስጥራዊነት ከመጠበቅ እንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚጣሉ እግዶችን ለማለፍ የሚረዱ ቢሆንም አስተማመመኝ ያልሆኑ ቪፒኤኖች ለመረጃ መንታፊዎች ሊያጋልጡን ይችላሉ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
