የጥላቻ ንግግርን አሉታዊ ሚና በመከላከል ረገድ የሚዲያዎች ሚና

The role of the media in preventing the negative role of hate speech

ጥር 19፣ 2016 ዓ.ም

የምክክሮች አደናቃፊ ሳንካዎችን በመዋጋት ረገድ ሚዲያዎች ቀዳሚ ሚና መወጣት እንዳለባቸው ብዙዎች ይስማማሉ።

ከዚህ አኳያም ሚዲያዎች የሚከተሉትን አወንታዊ አስተዋጾዎችን መወጣት ይችላሉ:

– ፕሮግራሞቻቸውን ከጥላቻ ንግግር ማጽዳት: ሚዲያዎች የሚሰሯቸው ፕሮግራሞች ከየትኛውም አይነት የጥላቻ ንግግር የጸዱ እንዲሆኑ ንቃት የታከለበት የክትትልና የአርትዖ ስራ መስራት ይገባቸዋል። ይህንን ለማድረግም ለጋዜጠኞች፣ለአዘጋጆች እና ለአርታዒያን ተከታታይነት ያለው የስልጠናና የምክክር መርሐግብሮችን ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ከጥላቻ ንግግር የጸዱ ፕሮግራሞችን በማቅረብ አርዓያ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

– ንቃትን ማሳደግ: ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግርን ምንነት እና የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በማስረዳት በማህበረሰቡ ዘንድ ንቃትን ማሳደግ ይገባቸዋል። በዚህም በጥላቻ ንግግር የማይሳተፍ፣ የማያበረታት፣ እንዲሁም የሚታገል ማህበረሰብ እንዲፈጠር አወንታዊ አስተዋጾ ማበርከት ይችላሉ።

– የምክክር መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀት: ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግርን በተመለከተ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም የተለያየ አመለካከት ያላቸው አካላት የሚሳተፉባቸው ውይይቶችን፣ ምክክሮችን፣ ቃለመጠይቆችን እና ተሞክሮዎች የሚያሳዩ መርሐግብሮችን በማዘጋጀት የጋራ ግንዛቤ ብሎም የመፍትሄ ሀሳቦች የሚፈልቁበትን አውድ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

– የአካታችነት ምሳሌ መሆን: ሚዲያዎች በሚሰሯቸው ፕሮግራሞች ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች እና ሁሉንም አይነት አመለካከቶች እንዲሳተፉ በማድረግ አካታች የሆነ ምህዳር መፍጠር ይችላሉ። ይህም አግላይና ለጥላቻ ንግግር በር ከፋች የሆኑ መደላድሎችን ለመጋፈጥ ይረዳል።

– ተጠያቂነትን ማስፈን: ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግር አድራጊ እና አሰራጭ ግለሰቦችን እንዲሁም ተቋማትን በንቃት በመከታተል እና በመመርመር ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ተጠያቂነትን በማስፈን የጥላቻ ንግ ግርን ስርጭት እንዲቀንስ ጉልህ ሚና ይጫወታል።
ከላይ የተዘረዘሩትን አዎንታዊ አስተዋጾውችን በመወጣት የሚዲያ ተቋማት የተሻለ ግንዛቤ ያለው እንዲሁም ከጥላቻ ንግግር የጸዳ ማህበረሰብና ከባቢ በመፍጠር ለሀገራዊ ምክክርና መግባባት ቁልፍ ሚና ማበርከት ይችላሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::