በአዲሱ አመት የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቀነስ የበኩላችንን አዎንታዊ ሚና እንወጣ
ጳጉሜን 04፣ 2016 ዓ.ም
አዲሱን አመት ልንቀበል ዋዜማው ላይ እንገኛለን። ልንሸኘው አንድ ቀን የቀረን አሮጌው አመት እንዳለፉት ሁሉ ለቁጥር ለሚታክቱ የሀሰተኛ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግ ግሮች፣ የማጭበርበር ድርጊቶች እንዲሁም የሴራ ትንታኔዎች የተጋለጥንበትና የተጋፈጥንበት ነበር።
እነዚህ አሉታዊ ይዘቶች አብሮነትና መቻቻል መሸርሸራቸው፤ መተማመንን ማላላታቸው፤ ግጭቶችን ማባባሳቸው፤ የገንዘብና የንብረት ጉዳትን ማድረሳቸው ሁላችንም የታዘብነው መራር ሀቅ ነው።
አንዳንዶቻችን የእነዚህን አሉታዊ ይዘቶች ስርጭት ለመግታት ብዙ ጥረናል። ሆኖም በተፈለገ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት የብዙ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ የግድ ይላል። ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሲቪክ ድርጅቶች፣ መንግስት እንዲሁም የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ደግሞ በዚህ ረገድ ውዴታም ግዴታም አለባቸው።
በአዲሱ አመት የሀሰተኛ መረጃን ጨምሮ የአሉታዊ ይዘቶችን ስርጭት ለመቀነስ ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሚጠበቅባቸውን አስተዋጾ ለማድረግ ቃል የሚገቡበት ሊሆን ይገባል። ማድረግ ከሚችሉት አዎንታዊ አስተዋጾ ዋነኛው አሉታዊ ይዘቶችን አለማመንጨት፣ አለማጋራት፣ አለማበረታታት ብሎም ማጋለጥና ማስተማር ይሆናል። ይህን በማድረግ ብቻ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ።
በተመሳሳይ የሚዲያ ተቋማት አሉታዊ ይዘቶችን በተለየ ትኩረት መከታተልና ማጋለጥን እንዲሁም የሚዲያ ንቃት ስራዎችን መስራት የአዲሱ አመት አንድ የትኩረት አቅጣጫ አድርገው መስራት ይጠበቅባቸዋል። የመረጃ አጣሪ ዴስክ ማቋቋም አልያም ባለሙያ መመደብ ደግሞ ቀናው መንገድ ይሆናል።
የሲቪክ ማህበራት በበኩላቸው የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ላይ ትኩረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎችን፣ ስልጠናዎችን፣ ዘመቻዎችን እና ጉትጎታዎችን በማድረግ ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀት ይገባቸዋል።
በአዲሱ አመት የሀሰተኛ መረጃን ጨምሮ የአሉታዊ ይዘቶችን ስርጭት ለመቀነስ መንግስት ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል። በተለይም አሉታዊ ይዘቶችን የሚያሰራጩ አካላትን በመቆጣጠር ረገድ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በራቀ እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማይጋፋ መልኩ የራሱን አስተዋጾ መወጣት ይገባዋል።
የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭዎች ባለፉት አመታት በተከተሉት የላላ ቁጥጥርና ክትትል ብሎም ቸልተኝነት ይደረሰውን የከፋ ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል
በአጠቃላይ የሀሠተኛ መረጃን ጨምሮ የአሉታዊ ይዘቶችን ስርጭት እንዲሁም የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የሁላችንን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን በመገንዘብ በአዲሱ አመት ጥረታችንን ከፍ ለማድረግ ቃል የምንገባበት ይሁን።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::