የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ስለ ኤርትራ ተናገሩት ተብሎ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ ነው

ሐምሌ 26፣ 2015 ዓ.ም
ሰሞኑን የሩስያ-አፍሪካ ስብሰባ በሴይንት ፔተርስበርግ ከተማ በተከናወነበት ወቅት የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ስለ ኤርትራ ተናገሩ ተብሎ በስፋት እየተሰራጨ ያለ መረጃ እንዳለ ተመልክተናል።
ይህ መረጃ በተለይ በትግራይ ቴሌቭዥን ተደጋግሞ የቀረበ ሲሆን ሚድያው ከሁለት ቀን በፊት “የአፍሪካ የሰላም እጦት ምክንያት ሽብርተኝነትና አለመረጋጋት ነው፣ እንደ ኤርትራ ያሉ ትናንሽ አገራት ደግሞ ይሄን ጉዳይ በማበረታታት ዋነኛ የአፍሪካ የሰላም እጦት ምክንያት እየሆኑ ነው ሲሉ የሴኔጋል ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ገለጹ” የሚል ዜና አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ቼክ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ንግግር ሲያደርጉ የሚታይበትን ይህን ቪድዮ መመልከት የቻለ ሲሆን ስብሰባውን ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዘኛ ሲተረጉም የነበረ አስተርጓሚ የቃላት ስህተት በመፈፀም የሰራው ስህተት እንደሆነ መገንዘብ ችለናል (ከ3:21:25 ጀምሮ https://www.youtube.com/live/-o2AT-thLgM?feature=share)
በዚህም መሰረት “Nous avons de micro états, hérités du congrès de Berlin” ብለው የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት በፈረንሳይኛ ያደረጉት ንግግር ወደ እንግሊዘኛ በትክክል ሲተረጎም “We have micro state that we inherited from Berlin Congress” ይሆናል።
ይሁንና አስተርጓሚው “hérité” ወይም በእንግሊዘኛ “inherited” የሚለውን ቃል “Eritrea/ኤርትራ” ወደሚል የተሳሳተ ትርጓሜ እንደሰጠው ተመልክተናል፣ ይህም እንደ ትግራይ ቴሌቭዥን ላሉ የተሳሳተውን የእንግሊዘኛ ትርጓሜው በቀጥታ ለወሰዱ ሚድያዎች መሳሳት ምክንያት ሆኗል።
ፕሬዝደንት ማኪ ሳል ይህንን ንግግር ስለ ኤርትራ ባያደርጉም ሀገሪቱ በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እና በአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት በቀጠናው ችግር ፈጣሪ እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ የተሰማራች ሀገር እንደሆነች ትጠቀሳለች።
በተለይ በቅርቡ በሰላም ስምምነት በበረደው የሰሜን ኢትዮጵያው አስከፊ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በርካታ ወንጀሎችን በትግራይ ክልል እንደፈፀሙ በርካታ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። የኤርትራ መንግስት ግን እነዚህን ክሶች ደጋግሞ ሲያጣጥል ይሰማል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
