ትናንት ምሽት በመስቀል አደባባይ ‘ድንገተኛ አደጋ’ እንደደረሰ በማህበራዊ ሚድያ የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው

ትናንት ምሽት በመስቀል አደባባይ 'ድንገተኛ አደጋ' እንደደረሰ በማህበራዊ ሚድያ የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው

መስከረም 17፣ 2018

በመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በድምቀት ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል ዳመራ በዓል በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደባባይ ተከብሯል።

ይህን በዓል አስታኮ ‘Yared Hiruy- ያሬድ ህሩይ’ በሚል ስም የተከፈተ እና ከ102,000 በላይ ተከታታዮች ያሉት የፌስቡክ ገፅ ትናንት ምሽት ብዙዎችን ያነጋገረ መረጃ አሰራጭቶ እንደነበር ተመልክተናል።

ገፁ በዚህ መልዕክቱ በመስቀል አደባባይ ትናንት በርካቶች እንደተጎዱ ገልፆ ህዝብ ፀሎት እንዲያደርግላቸው ይጠይቃል።

“ከመሸ በመዲናችን አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ ድንገተኛ አደጋ መድረሱን እየሰማን እንገኛለን። በርካታ አምቡላንሶች የተጎዱ ግለሰቦችን ወደ ሆስፒታል እያመላለሱ ነበር” የሚለው ገፁ በርካታ የፀጥታ አካላትም በስፍራው እንደሚገኙ ይገልፃል።

እዚህ የፌስቡክ ፅሁፍ ላይ 6,700 ሰዎች ሪአክት ያረጉ ሲሆን ከ440 በላይ ሰዎችም ግብረ-መልስ ሰጥተዋል።

ከዚህ መረጃ ጋር አብሮ አንድ ቪድዮ የተለቀቀ ሲሆን ቪድዮው በርካታ ሰዎች ሲራሯጡ እና ጭስ ወደ ሰማይ ሲለቀቅ ያሳያል (https://www.facebook.com/share/v/1Sk7t6BW1t/)

ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ዙርያ ማጣራት ያደረገ ሲሆን መረጃው ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጧል።

የድምፅ መረጃው መስከረም 3/2018 ዓ.ም ለህዳሴ ግድብ የድጋፍ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ትርዒት ሲለማመዱ የነበሩ ታዳጊዎች ላይ የደረሰ የመድረክ መደርመስ አደጋን አስታኮ ከተሰራ ዜና ተቆርጦ የተወሰደ መሆኑን ለማየት ችለናል።

ከዛም ድምፁን መስቀል አደባባይ ያልሆነ ቦታ ላይ የነበረን ከፍተኛ ጭስ የሚያሳይ ቪድዮ ላይ በመቀጠል መቀነባበሩን ተመልክተናል።

በተጨማሪም በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደባባይ በነበረው ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ የነበሩ በርካታ ግለሰቦችን አነጋግረናል፣ መንግስታዊ እና የፖሊስ መረጃዎችንም ለማየት ጥረናል።

ይሁንና አንድም ይህን መረጃ የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም፣ በዚህም መሰረት ተቀናብሮ የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ማየት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::