“አምባሳደር ሀመር የትግራይ፣ የአማራ እና የኦሮሞ ፖለቲካን ‘የሞት ትራያንግል’ በማለት ጠርተውታል” በሚል ርዕስ አልጀዚራ የሰራው ዘገባ የለም
ግንቦት 20፣ 2016
ከ13,600 በላይ ተከታዮች ያሉት እና ‘Pulp Faction’ የሚል ስያሜ የሚጠቀም የትዊተር አካውንት ከአልጀዚራ ድረ-ገጽ የተወሰደ የሚመስል የስክሪን ቅጅ (screenshot) ማጋራቱን ተመልክተናል።
በስክሪን ቅጅው ላይም “Ambassader Hammer Calls Tigray, Amhara and Oromo Politics in Ethiopia, The Triangle of Death” ወይም ወደ አማርኛ ሲተረጎም “አምባሳደር ሀመር የትግራይ፣ የአማራ እና የኦሮሞ ፖለቲካን ‘የሞት ትራያንግል’ በማለት ጠርተውታል’ የሚል አርዕስተ ዜና ይነበባል።
በዚሁ የስክሪን ቅጂ ላይም ጽሁፉ እ.አ.አ ግንቦት 17፣2024 ዓ/ም መታተሙን የሚገልጽ ቀን አመላካች መስመር (dateline) ይታያል። መረጃው እውነት ነው ብለው ያመኑ በርካታ ሰዎችም አስተያየቶቻቸውን ሲጽፉ አስተውለናል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ስክሪን ቅጂው ኤዲት ተደርጎ የተሰራ (doctored image) መሆኑን አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ ቼክ የስክሪን ቅጅውን ትክክለኛን ለማረጋገጥ በአልጀዚራ ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ማህደር (Ethiopia Archive) በጥልቀት የፈተሸ ሲሆን አልጀዚራ ከላይ የተጠቀሰውን አርዕስተ ዜና በመጠቀም የሰራው ምንም አይነት ዘገባ አለመኖሩን ተመልክተናል።
በስክሪን ቅጅው ላይ ስማቸው የተጠቀሰው አምባሳደር ማይክ ሀመር የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሆናቸው ይታወቃል።
ኤዲት ተደርገው የሚሰራጩ ስክሪን ቅጅዎች ለሀሠተኛ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ማጣራት እናድርግ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::