የግብፅ አምባሳደር በኤርትራ አድርገው መቐለ እንደገቡ በስፋት እየተጋራ የሚገኘው ምስል ላይ የሚታዩት ግለሰብ ህንዳዊ የህክምና ባለሙያ ናቸው
ጥቅምት 7፣ 2018
አንዳንድ የፌስቡክ እና ኤክስ (X) ተጠቃሚዎች “የግብፅ አምባሳደር በኤርትራ አድርጎ መቀሌ ገባ” በሚል ስክሪን ቅጂው የሚታየውን ምስል እንዲሁም ቪዲዮ እያጋሩ ይገኛሉ።
ይህን መረጃ እና ቪዲዮ ካጋሩ የፈስቡክ ገጾች መካከል ‘Triangle of Afar’ የሚል ስም እና ከ265 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ገጽ ይገኝበታል።
ይህ ገጽ ባጋራው ቪዲዮ ውስጥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ ታደሰ ወረደ፤ የህወሐት አመራር ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች ከአንድ የውጭ ዜጋ ጋር ሲወያዩ ይታያል።
ይህ በ‘Triangle of Afar’ የፌስቡክ ገጽ የተጋራ ቪዲዮ ከ860 ሺህ በላይ እይታ ያገኘ ሲሆን ከ600 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ደግሞ መልሰው አጋርተዉታል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ‘Habtish’ የሚል ስም ያለው የ ‘X’ አካውንት መረጃዉን ያጋራ ሲሆን “የግብጽ አምባሳደር” ብሎ የጠራው ይህ የውጭ ዜግነት ያለው ግለሰብ ከህወሐት ከፍተኛ አመራሮች ጋር እየተወያየ መሆኑንና የኢትዮጵያ መንግስትም ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጽፏል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ እና ቪዲዮው ላይ ባደረገው ማጣራት በምስሉ የሚታየው የውጭ ሀገር ዜጋ የግብፅ አምባሳደር አለመሆኑን አረጋግጧል።
ከትግራይ ክልል እና ህወሐት አመራሮች ጋር ሲነጋገር የሚታየው ግለሰብ የህንድ ሀገር ዜጋ ሲሆን ቪዲዮው የተቀረጸዉም ከአንድ ወር በፊት በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ተዋጊዎች የህክምና አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ነው።
በወቅቱ ስለ ፕሮግራሙ ከዘገቡ ሚዲያዎች መካከል ድምፀ ወያኔ አንዱ ሲሆን “የግብፅ አምባሳደር” በሚል ምስላቸው ከአውድ ውጭ የተጋራው እና ሌሎች ከህንድ የመጡ ህክምና አባላት ምስል እና ቪዲዮ ሚዲያው በሰራቸው ዘገባዎች ውስጥ ይታያሉ፡ ሊንክ እና ሊንክ
በተመሳሳይ ሁኔታ መቐለ ኤፍ ኤም 104́.4 በወቅቱ ስለ ህክምና ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የዘገበ ሲሆን “የግብፅ አምባሳደር” በሚል ሀሰተኛ መረጃ የተጋራባቸው ህንዳዊ ምስል በሬድዮ ጣቢያው የፌስቡክ ዘገባ ውስጥ ይገኛል፡ ሊንክ
እነዚህ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ህንዳዊው የህክምና ባለሙያ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት እጃቸው እና እግራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ተዋጊዎች ህክምና በሚያገኙበት ጉዳይ ዙርያ በመቐለ ውይይት ተደርጓል፣ ምስሉ ላይ የሚታዩትም የኦርቶፔዲክ ህክምና ባለሙያ ናቸው።
ህክምናውን ለማገዝ ሶስት ባለሙያዎች ወደ ህንድ በመጓዝ ትምህርት አግኝተው መመለሳቸውም ተጠቅሷል።
ከሌላ ቦታ ተወስደው ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ለተሳሳቱ እና ሀሰተኛ መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::