እነዚህ የጦር መሳርያዎች በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ስር የዋሉ አይደሉም

ነሐሴ 09፣ 2015 ዓ.ም
ከታች የሚታዩት በርከት ያሉ የጦር መሳሪያዎች ምስሎች ከትናንት በስቲያ (ነሐሴ 07/2015) ጀምሮ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወሩ ተመልክተናል።
በርካታ የፌስቡክ አካውንቶች እና ገጾች ምስሎቹ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከተከሰተው የጸጥታ ችግርና ግጭት ጋር በተገናኘ ቁጥጥር ስር የዋሉ የጦር መሳሪያዎች እንደሆኑ በሚገልጽ መልኩ እያጋሯቸው ይገኛሉ።
ምስሎቹን ያጋሩት አብዛኞቹ አካውንቶችና ገጾች “በአማራ ክልል በቆቦ ከተማ በሽፍታው ምሬ ወዳጆ ቤት በተደረገ ፍተሻ የተገኘ የጦር መሳሪያ ነው። አዎ ጀዊሳውን ጦር አስፈትቶ የአማራን ክልል የማፅዳት እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል።የክልሉ ህዝብ መከላከያ ከገባ ጀምሮ ወደ ተረጋጋ ሰላሙ እየተመለሰ ይገኛል” የሚል ተመሳሳይ መረጃም አብረው እያጋሩ ይገኛሉ።
አንዳንድ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም ምስሎቹ ከሰሞኑ ቁጥጥር ስር የዋሉ የጦር መሳሪያዎችን የሚያሳዩ እንደሆኑ በማሰብ ስለ ምስሎቹ ሀሳብና አስተያየታቸውን ሲሰጡም ተመልክተናል።
ይሁን እንጂ ምስሎቹ በአማራ ክልል ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር በተገናኘ ከሶስት ወራት በፊት የተነሱ እንደሆኑ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ ላይ ባደረገው ማጣራት መረዳት ችለናል።
በርካታ የመንግስት ተቋማት እንዲሁም መገናኛ ብዙኃንም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሚያዝያ 22፣ 2015 ያወጣውን መግለጫ በመጥቀስ ምስሎቹን አጋርተው ነበር።
ከነዚህ መካከልም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ “በዚህ ህቡዕ አደረጃጀት ውስጥ ሲንቀሳቀሱና የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 47 ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያዎች፣ ቦንቦችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንዲሁም ከሳተላይት መገናኛ መሣሪያዎች እና የተለያዩ መረጃዎችን ከያዙ ላፕቶፖች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አመልክቷል” ሲል የጦር መሳሪያዎቹን ምስል ከመግለጫው ጋር መማያያዝ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ አጋርቶ ነበር፡ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid0NSn6MXbofsbBTVae1fu6kL2uWophrPy62S1H8BQYZuTsMpK2zz3guJKfRhX32Kx8l&id=100064451782216&mibextid=qC1gEa
በተጨማሪም በተመሳሳይ ወቅት በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች “በቆቦ ከተማ በእነ መሬ ቤትና በከተማው ለህገወጥ ድርጊት የተከማቸና በአሳሰ የተገኝ” በሚል ምስሎቹን አጋርተው ነበር።
የኹነቶችን ጊዜ ሳይጠቅሱ እንዲሁም አውዳቸዉን በሳተ መልኩ የሚጋሩ ምስሎች እና መረጃዎች ለሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን እንዲሁም ለተሳሳተ ግንዛቤ ሊዳርጉን ስለሚችሉ ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
