እነዚህ ምስሎች ትግራይ ክልል ተመርቶ ሲጓጓዝ የነበረና ሰሞኑን ቁጥጥር ስር የዋለ የፋኖ ዩኒፎርም አያሳዩም
መስከረም 30፣ 2018
በርከት ያሉ የፌስቡክ አካውንቶች እና ገጾች መነሻዉን መቐለ አድርጎ ሲጓጓዝ የነበረ የፋኖ ታጣቂ ቡድን ዩኒፎርም በቁጥጥር ስር ውሏል የሚል መረጃ እና ምስሎችን እያጋሩ ይገኛሉ።
እነዚህ ማህበራዊ ትስስር ገጾች እና አካውንቶች በርከት ያሉ ቦንዳ ጥቅሎች እና የዕቃ ጭነት ተሽከርካሪ ከፊል አካልን የያዙ ምስሎችንም አጋርተዋል።
በተጨማሪም በቁጥጥር ስር የዋለዉ ዩኒፎርም ትግራይ ክልል ውስጥ በአልመዳ ጨርቃጨርቅ የተመረተ እንደሆነ እነዚህ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ጠቅሰዋል።
ምስሎቹን ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ‘Mahari T Hagos’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽ አንዱ ሲሆን ከ90 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃውን መልሰው አጋርተዉታል። በተመሳሳይ ‘ዲጂታል ኢትዮጵያ’ የተባለ ገፅ አጋርቶት ተመልክተናል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሎቹ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ ሰሞኑን የተነሱ እንዳልሆኑ አረጋግጧል። ምስሎቹ ትግራይ ክልል ተመርቶ ሲጓጓዝ የነበረ የፋኖ ዩኒፎርምን እንደማያሳዩም ተመልክተናል።
ምስልን በምልሰት መፈለጊያን መተግበርያ በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሎቹ ከ4 ዓመታት በፊት የተነሱ ሲሆኑ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከሆሳዕና ከተማ በቡታጅራ መስመር አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሊገባ የነበረ ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቆች ምስል ነው።
ይህ ኮንትሮባንድም በፌደራል ፖሊስ ፀረ-ኮንትሮባንድ አባላት ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን መረጃዉን እና ምስሎቹንም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ አጋርቶ ነበር፡ https://www.facebook.com/share/1BHC495gAY/?mibextid=wwXIfr
የቆዩ እና ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::