ቆየት ያሉ ይዘቶችን ለመፈለግ የሚረዳ መገልገያ

twitter verification

ጥቅምት 11፣ 2017 ዓ.ም

በቅርብ የተከሰተ እውነታን ለመደበቅ ቆየት ያሉ ይዘቶችን ማጣቀሻ ማድረግ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ ሀሠተኛ መረጃን የማሰራጫ ስልት መሆኑን ብዙዎቻችን ታዝበናል። ለምሳሌ በቅርቡ የተነሳን ፎቶ ወይም ቪዲዮ ለማስተባበል ያሰበ ሰው ከዓመታት በፊት በእከሌ ገጽ ተጋርቶ ነበር በማል ብቅ ሊል  ይችላል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደቆየው ይዘት የሚያደርስ ማስፈንጠሪያ (link) ከማያያዝ ይልቅ የስክሪን ቅጅ (screenshot) ብቻ ይለጥፋሉ። ይህም ግርታን ይፈጥራል።

ግርታችንን ለማጥፋት እና እውነታውን ለማወቅ ያለን ብቸኛ አማራጭ ከዓመታት በፊት በእከሌ ገጽ ተጋርቶ ነበር የተባለውን ይዘት ወደ ኃላ በመመለስ መፈለግ ይሆናል። ይህ ደግሞ ረዘም ያለ ጊዜና ፈጣን የኢንተርኔት ግንኙነት ሊፈልግ ይችላል።

በዚህን ጊዜ ነገሮችን የሚያቀልልን አጋር ያስፈልገናል። “ሁ ፖስትድ ዋት” (Who Posted What) የተባለው መገልገያ ደግሞ ለዚህ ተመራጭ ሲሆን በርከት ያሉ ተመራማሪዎች፣ ጋዜጠኞችና መረጃ አጣሪዎች ቆየት ያሉ ይዘቶችን ለመፈለግ በስፋት ይጠቀሙበታል።

“ሁ ፖስትድ ዋት” መገልገያ ለአጠቃቀም ቀላል ሲሆን በተለይም በፌስቡክ ተጋርተው የነበሩ እና ወራቶችንና ዓመታትን ያስቆጠሩ ይዘቶችን ለመፈለግ ይረዳል። ኢንስታግራምንና ኤክስ ትዊተርን በተመለከተም ውስን ድጋፎችን ይሰጣል።

በመገልገያውም ቁልፍ ቃላቶችን በተጋሩበት ቀን፣ ወር ወይም ዓመት አኳያ መፈለግ እንችላለን። ብሎም ቃላቶቹን በቀናት መካከል (timerange) ለመፈለግም ይረዳናል።  እንዲሁም የተጋሩበትን ቦታ መሰረት በማድረግ መፈለግ ያስችለናል።

በተጨማሪም ይዘቱን ያጋራውን ገጽ መሰረት አድርገን ወደኃላ ለመፈለግ ይረዳናል። ለፍለጋው ይረዳ ዘንድም መገልገያው የገጹን ልዩ መለያ ቁጥር (uid) እንድናውቅም ያመቻችልናል።

“ሁ ፖስትድ ዋት” የተሰኘውን ይህን መገልገያ ለመጠቀም ይህን ማስፈንጠሪያ ይከተሉ: https://whopostedwhat.com/

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::