የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ እውነተኛ እና ሀሰተኛ መረጃን የቀላቀለ የዜና ዘገባ

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ እውነተኛ እና ሀሰተኛ መረጃን የቀላቀለ የዜና ዘገባ

ሰኔ  18፣ 2016

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን (ኢቢሲ) ጨምሮ በርካታ ሚድያዎች “ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗ ተገለፀ” የሚል መረጃን አሰራጭተዋል።

መረጃዎቹ እንደጠቀሱት በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2023 ዓ/ም 3.26 ቢልዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በማግኘት ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ነች።

ይህም ትክክለኛ መረጃ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ (UNCTAD) ባሳለፍነው ሳምንት ያወጣውን ሪፖርት በመመልከት ማረጋገጥ ችሏል (ስክሪንሾት ተያይዟል)።

ይሁንና ኢትዮጵያ ይህን በምስራቅ አፍሪካ ያለ የአንደኝነት ደረጃን ያገኘችው አሁን ሳይሆን ላለፉት 12 አመታት ይዛው የቆየችው እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ (እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ ያለው መረጃ ባያያዝነው ስክሪንሾት ይታያል)።

ለምሳሌ እ.አ.አ በ2021 4.2 ቢልዮን ዶላር እና በ2022 3.6 ቢልዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አግኝታ ነበር፣ በዚህም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አንደኝነቷን ብታስጠብቅም ዘንድሮ የተገኘው 3.26 ቢልዮን ዶላር ከባለፉት ሁለት አመታት ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ እንዳሳየ ማየት ይቻላል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢቢሲ “ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያን ይከተላሉ” ብሎ በገባው ላይ አክሏል።

ኢትዮጵያ ቼክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ ሪፖርት ላይ ባደረገው ምልከታ ይህ የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ አረጋግጧል።

ግብፅ 9.8 ቢልዮን ዶላር እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ 5.2 ቢልዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ከኢትዮጵያ የተሻለ አፈፃፀም እንዳሳዩ መረጃዎቹ በግልፅ ይጠቁማሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::